በሺዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያን በቴህራን አደባባይ ወጥተው በመንግስት ላይ ቁጣቸውን አስሰሙ
ትናንት ምሽት ከ2 የኢራን ዩኒቨርሲቲዎች የወጡ ተቃዋሚዎች የሀገሪቱ መንግስት የዩክሬንን አውሮፕላን መትቶ መጣሉን ከቀናት በኋላ ማመኑን በመቃወም ነው ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት፡፡
መንግስት 176 ሰዎች የሞቱበትን አውሮፕላን በስህተት መትቶ መጣሉን ከ 3 ቀን በኋላ ትናንት ጥር 02 ቀን 2012 ዓ.ም ነው ያመነው፡፡ ለዚህም ስህተት አሜሪካ የጦር መሪዋን ቃሲም ሱሌይማኒ በመግደል የፈጸመችው ትንኮሳ ምክኒያት መሆኑን ነው የኢራን መንግስት ያስታወቀው፡፡
መንግስት የፈጸመውን ድርጊት ደብቆ መቆየቱን የተቃወሙት ሰልፈኞቹ ሞት ለአምባገነኖች፣ ሞት ለውሸታሞች የሚል መፈክር ያሰሙ ሲሆን፣ የሀገሪቱን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ካሜኒን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከስልጣን እንዲወርዱ ጠይቀዋል፡፡
አውሮፕላኑ ከቴህራን ተነስቶ ወደ ዩክሬን ኬቭ በረራ በጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ነው በሚሳይል ተመትቶ የተከሰከሰው፡፡ በዚህም 82 ኢራናውያንና 63 ካናዳውያንን ጨምሮ 176 የሰባት ሀገራት ዜጎች ሞተዋል፡፡
ኢራን አውሮፕላኑን በሚሳይል የመታችው፣ በኢራቅ የአሜሪካ 2 የጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት ከፈጸመች ከጥቂት ሰዓታት በኋላ መሆኑ ድርጊቱ ከሁለቱ ሀገራት ውጥረት ጋር እንዲያያዝ ምክኒያት ሆኗል፡፡ የኢራን መከላከያ ትናንት ባወጣው መግለጫ አውሮፕላኑ የተመታበት ምክኒያት አሜሪካ ለጥቃት የላከችው እንደሆነ በመጠርጠር ነው ማለቱ ይታወሳል፡፡
የምሽቱን የኢራናውያን የተቃውሞ ሰልፍ አሞካሽተው በትዊተር ገጻቸው የጻፉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ለጀግናው እና በስቃይ ውስጥ ላለከው የኢራን ህዝብ” ብለው በጻፉት መልእክት ወደ ፕሬዝዳንትነት ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ከኢራን ህዝብ ጎን እንደሆኑና አስተዳደራቸው አሁንም ከህዝቡ ጋር መሆኑን እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ሰልፈኞቹ ወንጀሎኞች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡም ጠይቀዋል፡፡
የኢራኑፕሬዝዳንት ሀሰን ሮሀኒ፣ ሀገራቸው በተፈጸመው ስህተት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማት ባስታወቁበት ወቅት ጥፋተኞች ለፍርድ እንደሚቀርቡ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡
ምንጭ፤- ሮይተርስ