የአሜሪካና ኢራን ፍጥጫ ለመካከለኛው ምስራቅ ሌላ ስጋት ደቅኗል
በኦባማ የመጨረሻ የፕሬዝዳንትነት ዘመን አሜሪካና ኢራን የተሻለ መግባባት ፈጥረው የገላጋዮቻቸውን አንተም ተው አንቺም ተይ ተማጽኖ በመስማት ሰላምን ወደማውረድ ቢንደረደሩም፣ የትራምፕ ወደ ዙፋን መምጣት የሰላም ተስፋዎችን ሁሉ መና አስቀርቷል፡፡
ካለፈው ሳምንት ወዲህ ሁለቱ ሀገራት አንድ ሁለት ተባብለው ፍጥጫቸው አይሏል፡፡ ትራምፕ ከሰሞኑ ክስተቶች በኋላ ያለ ቅድመ ሁኔታ ከኢራን ጋር ለመደራደር ዝግጁ እንደሆኑ መግለጻቸው እንደ ተስፋ ሰጪ ምልክት ቢታይም ኋላ ላይ ግን 176 ሰዎች የሞቱበት የዩክሬን አውሮፕላን በኢራን ሚሳይል ተመቶ ስለመከስከሱ ሀገሪቱም ጭምር ማመኗ የውጥረቱን አድማስ የሚያሰፋ ሌላ ክስተት ሆኗል፡፡ ኢራን በአሜሪካ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ አሜሪካ ልታጠቃኝ የላከችው የጦር አውሮፕላን ይሆናል በሚል በስህተት መትቼ ጣልኩት ያለችው የተሳፋሪዎች አውሮፕላን ጉዳይ ለሀገሪቱ ሌላ ጭንቀት ሆኖባታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ከህዝቧም ተቃውሞ እየገጠማት ነው፡፡ አሜሪካም በኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ጥላለች፡፡