ኢራን ከተከሰከሰው አውሮፕላን ጋር በተያያዘ እርምጃ መውሰድ ጀመረች
ኢራን በስህተት መትቼ ጥዬዋለሁ ካለችው የዩክሬን አውሮፕላን ጉዳይ ጋር በተያያዘ በርካታ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውያለሁ አለች፡፡
በስህተት ተፈጸመ ከተባለው ከዚህ ድርጊት ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን ከመግለጽ ውጭ የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ያለው ዝርዝር ነገር የለም፡፡
የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ ጎላምሆሴን ኢስማኢል እንዳሉት ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ የሚደረገው ምርመራ እንደቀጠለ ነው፡፡
የምርመራ ሂደቱ በልዩ ፍርድ ቤት እንደሚካሄድ የገለጹት ደግሞ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሮሀኒ ናቸው፡፡
የዩክሬን አለማቀፍ አየር መንገድ የበረራ ቁ. PS752 አውሮፕላን ባለፈው ሳምንት በኢራን ሚሳይል ተመቶ በመከስከስ 176 ሰዎች መሞታቸው ይታወቃል፡፡ ከሟቾቹም አብዛኛው ኢራናውያን እና ካናዳውያን ናቸው፡፡
ኢራን አውሮፕላኑ ከተከሰከሰ ከሶስት ቀናት በኋላ በስህተት በሚሳይል መትታ እንደጣለችው ይፋ ማድረጓ ይታወሳል፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ