ሶስት መርከቦቿ በኤርትራ የተያዙባት አዘርባጃን ቅሬታ አቀረበች
አዘርባጃን አዲስ አበባ እና ሩሲያ በሚገኙት ኢምባሲዎቿ በኩል ለኤርትራ ዲፕሎማሲያዊ መልእክት መላኳን ገልጻለች
ሶስቱ መርከቦች እና 18 ሰራተኞቻቸው ባጋጠማቸው አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ምክንያት ወደ ኤርትራ የውሃ አካል ከገቡ በኋላ በቁጥጥር የስር ውለዋል
ሶስት መርከቦቿ በኤርትራ የተያዙባት አዘርባጃን ቅሬታ አቀረበች።
የአዘርባጃን ሰንደቅአላማ የሚያውለበልቡ ሶስት መርከቦቿና ሰራተኞቻቸው ከባለፈው ህዳር ወር ጀምሮ የተያዙባት አዘርባጃን ቅሬታ ማቅረቧን የአርዘባጃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አይዛን ሀጂዛዳ በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
ሀጂዛዳ ለሮይተርስ እንደተናገሩት ሶስት መርከቦች እና ሁሉም የአዘርባጃን ዜግነት ያላቸው 18 ሰራተኞቻቸው በሱይዝ ቦይ በኩል ወደ አቡዳቢ እየተጓዙ በነበረበት ወቅት ባጋጠማቸው አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ምክንያት ወደ ኤርትራ የውሃ አካል ከገቡ በኋላ ህዳር 7፣2024 በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በካስፒያን ማሪን ሰርቪስ ቢ.ቪ. የአዘርባጃን ቅርንጫፍ ስር የሚተዳደሩት ሲኤምኤስ ፋህሊያን፣ ሲኤምኤስ አይጂድ እና ሲኤም-3 የተባሉት ሶስት መርከቦች የኤርትራን ባለስልጣናት አግኝተው የነበረ ቢሆንም ዝርዝር መረጃ እንዳልሰጧቸው ሀጂዛዳ ገልጸዋል።
ቃል አቀባዩ አዘርባጃን እስሩን ከሰማች በኋላ አዲስ አበባ እና ሩሲያ በሚገኙት ኢምባሲዎቿ በኩል ለኤርትራ ዲፕሎማሲያዊ መልእክት ልከላች ብለዋል።
"ችግሩን ለመፍታት፣ መርከቦቹን እና ሰራተኞቻቸውን ለማስለቀቅ እና ህጋዊ የኮንሱላር ድጋፍ ለማድረግ ስራ እየተሰራ ነው" ሲሉ ተናግሯል ሀጂዛዳ።