“ሰሜን ኮሪያ ጎረቤረቶቿን ለመወርር የሚያስችል የጦርነት ዝግጅት እያደረገች ነው” - አሜሪካ
አሜሪካ የፒዮንግያንግ ወታደሮች በዩክሬን ጦርነት የውጊያ ልምድ እያዳበሩ ነው ስትል አስጠንቅቃለች
ሩሲያ በበኩሏ የጃፓን ፣ ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ተደጋጋሚ የጦር ልምምድ ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ አቅሟን እንድታጠናክር የሚገፋ ነው ብላለች
ሰሜን ኮሪያ በጎረቤቶቿ ላይ ጦርነት ለመከፍት የሚያስችል የጦርነት ዝግጅት እያደረገች እንደምትገኝ አሜሪካ አስጠነቀቀች፡፡
ባሳለፍነው ሰኞ የሚሳኤል ሙከራ ያደረገችው ፒዮንግያግ በበኩሏ የመካከለኛ ርቀት የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራው ራስን የመከላከል አቅምን ለማጎልበት የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን አስታውቃለች፡፡
ሀገሪቱ በዩክሬኑ ጦርነት ከሩሲያ ጎን ተሰልፎ በመዋጋት የውጊያ አቅሟን እያሳደገች ነው ያለችው ዋሽንግተን ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለች ስለመሆኗ ይፋ አድርጋለች፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ከከፈተችበት 2022 ጀምሮ በሩስያ እና ሰሜን ኮሪያ መካከል እያደገ የሚገኘው ትብብር የመከላከያ እና ደህንነት የጋራ ትብብርን ወደ ማድረግ አድጓል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ምክትል የአሜሪካ አምባሳደር ዶርቲ ካሚል ከ12 ሺህ በላይ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ከባለፈው ወር ጀምሮ በሩሲያ ኩርስክ ግዛት ከዩክሬን ጦር ጋር መዋጋት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በምላሹ ፒዮንግያንግ ሩሲያ ሰራሽ ጦር መሳሪያዎችን ፣ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎችን እና የውጊያ ልምድን በማካበት በጎረቤቶቿ ላይ ጦርነት መክፈት የሚያስችላትን አቅም ለመገንባት እየተጠቀመችበት ነው ብለዋል አምባሳደሯ፡፡
ከዚህ ባለፈም ሀገሪቱ አሁን በምትገኝበት ሁኔታ በአለም አቀፍ ደረጃ የጦር መሳሪያ ሽያጭ እና ወታደራዊ ስልጠና ውሎችን ለመፈጸም በሚያስችል አቅም ላይ እንደምትገኝ አሜሪካ አስጠንቅቃለች፡፡
የሰሜን ኮሪያው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አምባሳደር ኪም ሶንግ “በጋዛ ውስጥ ከ 45ሺህ በላይ ንጹሀን ሲሞቱ፣ አሜሪካ ይህን የእስራኤልን የጅምላ ግድያ ራስን የመከላከል መብት አድርጋ ስታስጌጥ ፤ የሰሜን ኮሪያን ራስን የመከላከል እንቅስቃሴ ህገወጥ አድርጋ ለመሳል መሞከሯ ፍትሀዊ አይደለም” ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
አሜሪካ ፣ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን በሰሜን ኮሪያ አቅራቢያ ተደጋጋሚ ወታደራዊ ልምምዶችን ማድረጋቸው ሀገሪቱ የጦር አቅሟን ማሳደግ ላይ እንድታተኩር አድርጓል ሲሉ የተናገሩት ደግሞ በተመድ የሩስያ አምባሳደር ቫዝሊ ኔቤንዚያ ናቸው፡፡
በተጨማሪም ሩሲያ የሳተላይት እና የጠፈር ቴክኖሎጂዎችን ለፒዮንግያንግ እያጋራች ነው በሚል የቀረበውን የአሜሪካን ውንጀላ “ሙሉ ለሙሉ መሰረተ ቢስ” ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።