አሮጌ መኪናውን እየነዳ ቱርካዊያንን ለመርዳት የመጣው አዘርባጃናዊ ቅንጡ መኪና ተሸልሞ ተመለሰ
ግለሰቡ ያሳየው ሩህሩህነት በቱርካዊያን ለመሸለም አብቅቶታል
በቱርክና ሶሪያ በደረሰው ርዕደ መሬት የሟቾች ቁጥር ከ50 ሺህ አልፏል
በርእደ መሬት የተጎዱ ቱርካዊያንን ለመርዳት የመጣው የአዛርባጂያን ዜጋ ቅንጡ መኪና ይዞ ተመለሰ።
በቱርክ ከሁለት ሳምንት በፊት በታሪክ ከፍተኛ የተባለ ርዕደ መሬት አደጋ መከሰቱ ይታወሳል። ይህ አደጋ በደቡባዊ ቱርክ እና ሰሜናዊ ሶሪያ የተከሰተ ቢሆንም አደጋው በአንጻራዊነት ቱርክን የበለጠ ጎድቷል።
በዚህ አደጋ ምክንያትም የሟቾች ቁጥር ከ50 ሺህ ያለፈ ሲሆን ተጎጂዎችን ለመታደግ ኢትዮጵያን ጨምሮ የዓለም ሀገራት ተረባርበዋል።
ይሁንና የቱርክ ጎረቤት ከሆነችው አዛርባጂያን መዲና ባኩ ከተማ በራሱ አሮጌ መኪና እርዳታዎችን ይዞ ወደ ቱርክ የመጣው ግለሰብ የብዙዎችን ልብ ነክቷል።
ግለሰቡ ድሀ የሚባል ቢሆንም ከቤተሰቡ እና ከጓደኞቹ ያሰባሰባቸውን አልባሳት እና ምግብ በመያዝ መምጣቱ ቱርካዊያንን አስገርሟል።
በዚህ ደግ አዛርባጂያን ድርጊት ልባቸው የተነካው የቱርክ አንድ ባለሀብት አዲስ ቅንጡ መኪና ሸልመውታል ሲል አናዶሉ ዘግቧል።
ግለሰቡ የ1980ዎቹ ስሪት የሆነች አሮጌ መኪናውን እያሽከረከረ የርእደ መሬት አደጋ ወደ ደረሰባቸው አካባቢዎች መምጣቱ እና የያዛቸውን ቁሳቁሶች ለተጎጂዎች ሰጥቷል ተብሏል።
በዚህም ምክንያት ግለሰቡ ያደረገው ድርጊት ሚዲያዎች ማስተጋባታቸውን ተከትሎ ዝናው ከቱርክ አልፎ ዓለም አዳርሷል ተብሏል።