በእስራኤል የአየር ጥቃት ከተገደለች እናት ማህጸን ህጻን በህይወት ወጣች
ሟች እናት በተገደለችበት የምሽት የአየር ጥቃት በድምሩ 19 ሰዎች ተገድለዋል
በጋዛዋ የራፋ ከተማ እስራኤል ባደረሰችው የአየር ጥቃት ከባለቤቷ እና ከሴት ልጇ ጋር ከተደገለች እናት ማህጸን ህጻን ልጅ በህይወት መውጣቷ ተገልጿል
በእስራኤል የአየር ጥቃት ከተገደለች እናት ማህጸን ህጻን በህይወት መውጣቷ ተነገረ።
በጋዛዋ የራፋ ከተማ እስራኤል ባደረሰችው የአየር ጥቃት ከባለቤቷ እና ከሴት ልጇ ጋር ከተደገለች እናት ማህጸን ህጻን ልጅ በህይወት መውጣቷን የፍልስጤም ጤና ባለስጣናት መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሟች እናት በተገደለችበት ከትናንት በስትያ ምሽት በደረሰው የአየር ጥቃት በድምሩ 19 ሰዎች ተገድለዋል።
ባለስልጣናቱ እንደገለጹት ከሆነ ሁለት ቤቶች ላይ በደረሰው የአየር ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 13 ልጆችም ግድያ ተፈጽሞባቸዋል።
1.4 ኪሎግራም የምትመዝነው እና በሲ-ሴክሽን ከሟች እናቷ ማህጸን የወጣችው ህጻን መረጋጋቷን እና ሁኔታዋ ቀስበቀስ እየተሻሻለ መሆኑን ክትትል የሚያደርጉላት ዶክተር ሞሀመድ ሰላማ ተናግረዋል።
ህጻኗ ከሌሎች ህጻናት ጋር በራፋ በሚገኘው ሆስፒታል ኢንኩቤተር ወይም ሙቀት መስጫ ማሽን ውስጥ እንድትሆን ተደርጓል ተብሏል።
በአየር ጥቃቱ የተገደለችው የሟች ሳብሪን ሰካኒ ሴት ልጅ የሆነችው ማሊክ አዲሷን እህቷን ሮህ ብላ ስም ለማውጣት ፈልጋ ነበር፤ ሮህ ማለት መንፈስ ማለት እንደሆነ አጎቷ ራሚ አል-ሼክ ገልጿል።
"ትንሿ ማሊክ እህት እንደሚወለድላት ስታቅ በደስታ ተሞልታ ነበር"
ዶክተር ሰላማ እንዳሉት ህጻኗ ከሶስት እስከ አራት ሳምንታት ሆስፒታል ውስጥ ትቆያለች።
"ከእዚያ በኋላ እንዴት እንደምትኖር እናያለን።ይህች ህጻን የት ነው እንደምትሄድ?፣ ወደ ቤተሰብ፣ ወደ አክስቷ፣ ወደ አጎቷ ወይስ ወደ አያቶቿ። አሳዛኙ ነገር ይሄ ነው። ህጻኗ ብትድንም፣ ወላጅ አልባ ሆና ነው የተወለደችው" ብለዋል ዶክተሩ።
እንደ ፍልስጤም የጤና ባለስልጣናት ከሆነ የአብደል አል ቤተሰብ በሚኖሩበት ሁለተኛው ቤት ላይ በተፈጸመው ጥቃት 13 ህጻናት ተገድለዋል።በዚሁ ጥቃት ሁለት ሴቶችም ገድለዋል።
በራፋ ስለደረሰው ጥቃት የተጠየቁት የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ወታራዊ ካምፖችን እና ማነጣጠሪያ ኬላዎችን እና ታጣቂዎችን ጨምሮ ወታደራዊ ኢላማዎች ተመተዋል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
"ከተገደሉት መካከል አንድ ወንድ አይተሀል?" ሲል አብደል አል የተገደለውን ህጻን ልጁን አስከሬን አቅሮ እያለቀሰ ይጠይቃል።
የተገደሉት "ሁሉም ሴቶች እና ህጻናት ናቸው" ያለው አብደል አል "ሁሉም ማንነቴ ከባለቤቴ እና ከልጆቹ ጋር እንዲጠፉ ሆነ" በማለት በምሬት ተናግሯል።
የጥቅምት ሰባቱን የሀማስ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ እየወሰደችው ባለው መጠነሰፊ የምድር እና የአየር ጥቃት ከ32ሺ በላይ ፍልስጤማውያንን መገደላቸው የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ተናግረዋል።