የእስራኤል ወታደራዊ ደህንነት ሀላፊ ዜጎችን ከጥቃት መከላከል አልቻልኩም በሚል ስልጣን ለቀቁ
ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ጦርነት ተከስቷል
በዚህ ጦርነት ከ33 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊን እና ከ1 ሺህ 200 በላይ እስራኤላዊያንም ተገድለዋል
የእስራኤል ወታደራዊ ደህንነት ሀላፊ ዜጎችን ከጥቃት መከላከል አልቻልኩም በሚል ስልጣን ለቀቁ፡፡
የእስራኤል ወታደራዊ ደህንነት ሀላፊ የሆኑት ሜጀር ጀነራል አሃሮን ሃሊባ ዜጎችን ከጥቃት መጠበቅ አልቻልኩም በሚል ስልጣን ለቀዋል፡፡
እንደ ሀገሪቱ ሚዲያዎች ዘገባ ከሆነ ሜጀር ጀነራል አሃሮን የፍልስጤሙ ሐማስ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ በእስራኤል ላይ ላደረሰው ጥቃት ሃላፊነት እወስዳለሁ ብለዋል፡፡
ሓላፊው ለእስራኤል መከላከያ በጻፉት የስልጣን መልቀቂያ ማመልከቻቸው ላይ “እኔ የምመራው የእስራኤል ደህንነት እያለ በእስራኤላዊያን ላይ ከባድ ጥቃት ተሰንዝሯል፣ ለዚህ እኔ ሃላፊነቱን እወስዳለሁ፣ ዕለቱም እድሜ ልኬን በሐዘን ሳስታውሰው እኖራለሁ፣ ጥቃቱ ከተፈጸመበት እለት ጀምሮ ቀንም ሆነ ሌሊት ሳስበው ነበር ለተፈጠረው ሀዘን እና ጥቃት ሁሉ ሃላፊነቱን እወስዳለሁ” ብለዋል፡፡
የሜጀር ጀነራል አሀሮን የስልጣን ልልቀቅ ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል ተብሏል፡፡
ሀላፊው የሐማስ ጥቃትን ተከትሎ ስልጣን የለቀቁ የመጀመሪያው ሰው ናቸው የተባለ ሲሆን በቀጣይ ሌሎች ተጨማሪ ሀላፊዎች ስልጣን እንደሚለቁ ይጠበቃል፡፡
ይሁንና ከሐማስ ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት ሳይጠናቀቅ ስልጣን መልቀቅ እንደማይገባ ወታደራዊ ባለሙያዎች ተችተዋል፡፡
የሀማስ ታጣቂዎች የአይሁዶች ልዩ በዓል ዕለት ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት ከ1 ሺህ 200 በላይ ዜጎችን ሲገደሉ 250 ሰዎች ደግሞ ታግተው ተወስደዋል ተብሏል፡፡
እስራኤል በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ከ33 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን ሲገደሉ ከሟቾች ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች እና ህጻናት እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
ሄዝቦላ በደቡባዊ ሊባኖስ የእስራኤልን ድሮን መትቶ ጣለ
ጦርነቱ አሁንም የቀጠለ ሲሆን እስራኤል ከሐማስ በተጨማሪ ከሂዝቦላህ፣ ሁቲ እና ኢራን ጋር የቀጥታ ጦርነት እያደረገች ትገኛለች፡፡
በርካታ ሀገራት እና የሰብዓዊ ድርጅቶች እስራኤል በፍልስጤማዊን ላይ እያደረሰች ያለውን ጥቃት እንድታቆም ግፊት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ይሁንና እስራኤል በሐማስ ላይ ድል መቀዳጀቷን ገልጻ ጥቃቱ ግን ይቀጥላል ስትል የተወሰኑ ሀገራት ደግሞ ሀገሪቱ በሐማስ ታጣቂዎች ስም በንጹሃን ላይ የጦር ወንጀል እየፈጸመች በመሆኑ በህግ ልትጠየቅ ይገባል በማለት ላይ ናቸው፡፡