እስራኤል ፍልስጤማውያን ወደ ሰሜናዊ ጋዛ እንዳይመለሱ አስጠነቀቀች
የእስራኤል ወታደሮች ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ለመግባት የሞከሩ 5 ፍልስጤናውያንን መግደላቸውና ከ54 በላይ ሰዎችን ማቁሰላቸው ተሰምቷል
በራፋህ ጦርነት ለመጀመር የመከረው የእስራኤል ጦር ፍልስጤማውያን ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ከተመለሱ ሃማስ ዳግም ራሱን ያደራጃል የሚል ስጋት አለው
የእስራኤል ጦር ፍልስጤማውያን ወደ ሰሜናዊ ጋዛ እንዳይመለሱ አስጠነቀቀ።
ከትናንት በስቲያ እሁድ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በእግራቸውና በአህያ በሚጎተቱ ጋሪዎች ተሳፍረው ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ሲጓዙ ታይቷል።
እስራኤል ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መፍቀዷን መረጃ እንደሰሙ የሚናገሩት ፍልስጤማውያን፥ ሰሜናዊ ጋዛን ከቀሪው የጋዛ ሰርጥ በሚለየው የዋዲ ጋዛ የፍተሻ ጣቢያ ሲደርሱ ግን ተኩስ እንደተከፈተባቸው ገልጸዋል።
በዚህም አምስት ፍልስጤማውያን መገደላቸውንና ከ54 በላይ መቁሰላቸውን በማዕከላዊ ጋዛ የሚገኘው የአውዳ ሆስፒታል አስታውቋል።
በትናንትናው እለት በራፋህ ለመጀመር ስለታሰበው ዘመቻ የመከረው የእስራኤል ጦር ስለፍልስጤማውያኑ ግድያ ያለው ነገር ባይኖርም ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ለመመለስ የሚደረገው ጥረት እንዲቆም አሳስቧል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት በራፋህ ጦርነቱን ለመጀመር ፍልስጤማውያን ወደተዘጋጀላቸው መጠለያ እንዲያመሩ ይደረጋል እንጂ ወደ ሰሜናዊ ጋዛ አይመለሱም ብለዋል።
1 ነጥብ 4 ሚሊየን ፍልስጤማያን በሚገኝባት ራፋህ ሃማስን የመደምሰስ ጦርነት ለመክፈት ዝግጅት ለማድረግ በጋዛ የሚገኝ ጦሯን የቀነሰችው እስራኤል የፍልስጤማውያኑ ወደ ሰሜናዊ ጋዛ መመለስ ሃማስን ዳግም እንዲደራጅ ያግዘዋል በሚል ትቃወመዋለች።
ሃማስ በተኩስ አቁም ድርድሮች ላይ የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የሚያቀርበውን ጥያቄ ውድቅ ስታደርግ መቆየቷም ይታወሳል።
ቴል አቪቭ ከራፋህ የምታስወጣቸውን ፍልስጤማውያን የት ለማስፈር እንዳሰበች ግን እስካሁን በግልጽ አልታወቀም።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ አቪቻይ አድራይም ፍልስጤማውያን “አደገኛ የጦር ቀጠና” ወደሆነው ሰሜናዊ ጋዛ ከመመለስ ይልቅ ባሉበት እንዲቆዩ ከማሳሰብ ውጭ በእስራኤል ወታደሮች ስለተከፈተው ተኩስ ያሉት ነገር የለም ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
የአይን እማኞች ግን በዋዲ ጋዛ የፍተሻ ጣቢያ ሴቶችና ህጻናት እንዲያልፉ ተፈቅዶ ወጣቶች ላይ ተኩስ መከፈቱን ተናግረዋል።
በእስራኤል ጥቃት በፈራረሰው ሰሜናዊ ጋዛ 300 ሺህ ፍልስጤማውያን በከባድ ሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ይገኛሉ።