ወታደሮቿን ከካን ዩኒስ ያስወጣችው እስራኤል ራፋህ የምትገባበትን ቀን ወስናለች
ስድስት ወራት ያስቆጠረውን ጦርነት ለማስቆም በካይሮ እየተካሄደ ያለው ድርድር ተስፋ ሰጪ ውጤት እንዳልተገኘበት ተገልጿል
ግብጽ፣ ፈረንሳይና ዮርዳኖስ በጋራ ባወጡት መግለጫ እስራኤል በራፋህ ልትጀምረው ያሰበችውን ጦርነት በጥብቅ ተቃውመዋል
እስራኤል በራፋህ እግረኛ ጦሯን በማስገባት ጦርነት የምትጀምርበት ቀን መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተናገሩ።
ኔታንያሁ የራፋህ ዘመቻ መቼ እንደሚጀመር ከማብራራት ቢቆጠቡም 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ፍልስጤማውያን የተጠለሉባት ከተማ የጦር አውድማ መሆኗ አይቀሬ መሆኑን ጠቁመዋል።
“በካይሮ እየተካሄደ ያለው ድርድር ዝርዝር ሪፖርት ደርሶኛል፤ ታጋቾችን ለማስለቀቅና በሃማስ ላይ ሙሉ ድል ለመቀዳጀት እየሰራን ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለዚህም ወደ ራፋህ መዝለቃችን የግድ ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
የእስራኤሉ መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንትም ታጋቾችን ለማስለቀቅ የሚያስችል ስምምነት ለመድረስ ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።
ሃማስ በበኩሉ እስራኤል የፍልስጤማውያንን ጥያቄ የሚመልስ አዲስ የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ እንዳላቀረበች ነው ያስታወቀው።
የቡድኑ ከፍተኛ አመራር አሊ ባራካ፥ የፖሊት ቢሮው ተሰብስቦ የእስራኤልን የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ ውድቅ እንዳደረገው ተናግረዋል።
የካይሮው ድርድር በቀጠለበት እለት ከእስራኤል የተሰማው የራፋህ ጦርነት እቅድ ስድስት ወራት በሰቆቃ ያሳለፉት ፍልስጤማውያን የከፋ መከራ ከፊታቸው መደቀኑን ያሳያል ተብሏል።
ግብጽ፣ ፈረንሳይ እና ዮርዳኖስም በደቡባዊ ጋዛ በምትገኘው ራፋህ የሚፈጸም ጥቃት “አደገኛ ቀውስ” ይፈጥራል በሚል እስራኤልን ተቃውመዋል።
የሀገራቱ መሪዎች በጋራ ባወጡት መግለጫም ቀን ተቆርጦለታል የተባለው የራፋህ ጦርነት “ከሞትና ስቃይ ውጭ የሚያስገኘው አንዳች ነገር የለም፤ ቀጠናዊ ውጥረትን ያባብሳል” ብለዋል።
የጸጥታው ምክርቤት እስራኤል በጋዛ በአስቸኳይ ተኩስ እንድታቆምና ሃማስም ታጋቾችን እንዲለቅ ያሳለፈው ውሳኔም ያለምንም መሸራረፍ ተፈጻሚ ሊሆን እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።
ይሁን እንጂ ከ33 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈውን ጦርነት ከዶሃ እስከ ካይሮና ፓሪስ የዘለቁ ድርድሮችም ሆኑ የጸጥታው ምክርቤት ውሳኔ ሊያስቆመው አልቻለም።