የዶክተር አንዱአለም ግድያ "ጥልቅና ግልጽ" ምርመራ እንዲደረግበት የሚጠይቅ ዘመቻ መከፈቱን ዩኒቨርስቲው አስታወቀ
የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ አባላት "ፍትህ ለዶክተር ለአንዱአለም ዳኜ" የሚል መፈክር በማሰማት ሰልፍ ማድረጋቸውን ዩኒቨርሲቲው በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል
ግድያውን ማን እንደፈጸመው እስካሁን ይፋ የሆነ ነገር የለም
የዶክተር አንዱአለም ግድያ "ጥልቅና ግልጽ" ምርመራ እንዲደረግበት የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ጠየቀ።
ከአራት ቀናት በፊት ከስራ ቦታ ወጥተው ቤታቸው አቅራቢያ ሲደርሱ በተተኮሰባቸው ጥይት የተገደሉት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲው ዶክተር አንዱአለም ጉዳይ በተለይ በህክምና ማህበረሰቡ ዘንድ ድንጋጤና ቁጣን ፈጥሯል።
የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ አባላት "ፍትህ ለዶክተር ለአንዱአለም ዳኜ" የሚል መፈክር በማሰማት ሰልፍ ማድረጋቸውን ዩኒቨርሲቲው በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል።
በዶክተሩ ሞት ምክንያት ጥልቅ ሀዘን ውስጥ መሆናቸውን ባወጡት መግለጫ የጠቀሱት የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አባላት "የዶክተር አንዱአለም ሞት ለዩኒቨርስቲው፣ ለህክምና ማህበረሰቡ እና እያገለገላቸው ላላቸው ታካሚዎች ትልቅ ጉዳት ነው"ብለዋል።
"ፈዋሽ እጆች በፍጹም በጠብመንጃ መኮላሸት የለባቸው" ያለው መግለጫው አለምአቀፉ ማህበረሰብ፣ የመብት ድርጅቶችና ለጤና ጥበቃ የቆሙ ቡድኖች "ፍትህ ለአንዱአለምና ለሌሎች የጤና ባለሙያዎች" በሚል የጀመረውን ዘመቻ እንዲቀላቀሉት ጥሪ አቅርቧል።
የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ በመግለጫው የዶክተር አንዱአለም ግድያ "ጥልቅና ግልጽ" ምርመራ እንዲካሄድበት፣ የጤና ባለሙያዎች የተሻለ ጥበቃ እንዲደርጥላቸውና የጤና አገልግሎት ገለልተኝነት መርህ እንዲከበርና በሰብዓዊ ስራቸው ኢላማ እንዳይደረጉ ጠይቋል።
ዶክተር አንዱአለም በባህርዳር ዩኒቨርስቲ በመምህርነት ከተቀጠሩ በኋላ ጎን ለጎን በዩኒቨርስቲው የቀዶ ህክምና ክፍል ተምረው በ2011 ዓ.ም ተመርቀው እውቅ የቀዶ ህክምና ባለሙያ መሆን መቻላቸውን ዩኒቨርስቲው ያወጣው የዶክተሩ የህይወት ታሪክ ጽሁፍ ያስረዳል።
ዶክተር አንዱአለም ቀጥሎም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጉበት፣ የሀሞት ከረጢትና የቆሽት ሰብ ስፔሻላይዜሽን ትምህርት ቤት በ2016 ዓ.ም ተመርቀው በማገልገል ላይ ያሉ ዕውቅ ሀኪም እንደነበሩም ታሪካቸው ይጠቅሳል።
ታሪካቸው እንደሚገልጸው "ዶክተር አንዷለም ዳኜ በተለያዩ የትምህርት እርከን ሲያልፉ በተለያዩ የውጭ ሀገራት ማለትም በጀርመን፣ በእንግሊዝ፣ በህንድ፣ በደ/አፍሪካ እና በቱርክ የተለያዩ ስልጠናዎችን የወሰዱና በዚህም ከፍተኛ ከበሬታን" ያተረፉ ናቸው።
በአማራ ክልል በፌደራል መንግስት የጸጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከሁለት አመት በፊት ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የህክምና ባለሙያዎች የተለያየ ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ የመብት ተቋማት ድርጅቶች ሪፖርት ማውጣታቸው ይታወሳል።
ግድያውን ማን እንደፈጸመው እስካሁን ይፋ የሆነ ነገር የለም።