የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ከፑቲን ጋር በቀጥታ ተገናኝተው መነጋገር እንደሚፈልጉ ገለጹ
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ከፑቲን ጋር በቀጥታ ተገናኝተው መነጋገር እንደሚፈልጉ ገለጹ
ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከዚህ ቀደም የሩሲያ ጦር ሙሉ ለሙሉ ከዩክሬን ሳይወጣ ድርድር እንደማይታሰብ ሲናገሩ ቆይተዋል
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ለማቆም ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በድርድር ጠረጴዛ ላይ ለመቀመጥ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
ፕሬዝዳንቱ ከፒርስ ሞርጋን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፑቲንን እንደ “ጠላት” እንደሚመለከቷቸው ገልጸው ነገር ግን “ለዩክሬን ህዝብ ሰላም የሚያመጣ ከሆነ ቀጥተኛ ድርድር ለማድረግ ዝግጁ ነኝ” ብለዋል፡፡
በድርድሩ ላይ ከሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ባለፈ አራት ታዛቢዎች እንዲሳተፉ እንደሚፈልጉ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ማንነታቸውን በይፋ ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
የዩክሬን እና ሩስያን ጦርነት ማስቆም ከዋና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎቻቸው መካከል አንዱ እንደሆነ የተናገሩት 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በጀመሩበት ወቅት ነው ዘለንስኪ ለድርድር ፈቃደኛነታቸውን ገልጸዋል፡፡
"ከፑቲን ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ ነኝ፤ ይህ ውይይት እንዴት እንደሚጀመር እና እንዴት እንደሚጠናቀቅ ማንም አያውቅም። ነገር ግን ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዚህ ውይይት ስኬታማ መሆን ይፈልጋሉ ብለን እናምናለን" ብለዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩሉ ግጭቱን ለማስቆም ለመነጋገር ዝግጁ ቢሆንም ከዘለንስኪ ጋር ቀጥተኛ ድርድር ማድረግ እንደማይፈልጉ ከቀናት በፊት ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ሩሲያ እንደቅደመ ሁኔታ ያስቀመጠቻቸው የግዛት እውቅና ጉዳይ እና የደህንነት ዋስትና አሁንም በድጋሚ በሞስኮ ባለስልጣናት ዘንድ ከድርድሩ በፊት መቋጨት ያለባቸው ጉዳዮች እንደሚሆኑ ትኩረት ተደርጎባቸዋል፡፡
የዲፕሎማሲ አማራጮችን ለመቃኘት ፈቃደኛ መሆናቸውን የገለጹት ዘለንስኪ ከዚህ ቀደም የሩስያ ጦር ሙሉ ለሙሉ ከዩክሬን ሳይወጣ ድርድር አይታሰብም የሚል አቋም ሲያንጸባርቁ ቆይተዋል፡፡
ኒውስዊክ በዘገባው የትራምፕ የዩክሬን ድጋፍ ማቋረጥ ዛቻ እና ከዴሞክራቱ ጆ ባይደን በተለየ ከወታደራዊ እገዛ ይልቅ የድርድር አማራጭ ላይ ማተኮራቸው ዘለንስኪ እንዲለሳለሱ ሳያደርጋቸው እንዳልቀረ ዘግቧል፡፡
የዩክሬን ተቀዳሚ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዩሊያ ስቪሪደንኮ በበኩላቸው "ጦርነቱ በዚህ አመት እንደሚያበቃ ተስፋ እናደርጋለን። ቅድሚያ የምንሰጠው ሰላምን ማስፈን ብቻ ሳይሆን ዩክሬን ወደ መደበኛ ህይወት እንድትመለስ የሚያግዙ ጠንካራ የደህንነት ዋስትናዎች ላይ መደራደር ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ቀጠናው ልዑካኖቻቸውን ከመላካቸው በፊት ከመሪዎቹ ጋር በቀጥታ ለመነጋገር አቅደዋል በቅርቡም ከሩስያው አቻቸው ጋር ሊነጋገሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡