ትራምፕ አሜሪካ ጋዛን የራሷ ማድረግ ትፈልጋለች አሉ
ትራምፕ ቀደም ሲል በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን በቋሚነት ወደ ሌላ ሀገር መዛወር አለባቸው የሚል አወዛጋቢ ሀሳብ ሰንዝረዋል
አሜሪካ የእስራኤልና ፍልስጤምን ሁለት ሀገርነት መፍትሄ ለበርካታ አስርት አመታት ስትደግፍ ቆይታለች
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራሜፕ በ16 ወራት የእስራኤልና ሀማስ ጦርነት የወደመችውን ጋዛን መውሰድ እንደሚፈልጉ ተናገሩ።
ትራምፕ ቀደም ሲል በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን በቋሚነት ወደ ሌላ ሀገር መዛወር አለባቸው የሚል አወዛጋቢ ሀሳብ ሰንዝረዋል።
ትራምፕ በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን ወደ ግብጽና ጆርዳን እንዲዛወሩ ያቀረቡት ሀሳብ በፍልስጤም አስተዳደር ባለስልጣናትና በአረብ ሀገራት ውድቅ የተደረገ ሲሆን የመብት ተሟጋቾችም ደግሞ ከዘርማጽዳት ጋር የሚስተካከል በሚል ተወግዟል።
ፕሬዝደንት ትራሞፕ ስለእቅዱ ዝርዝር ማብራሪያ አላቀረቡም።
ትራምፕ በኃይትሀውስ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በሰጡት መግለጫ "አሜሪካ የጋዛ ሰርጥን ትጠቀልላለች፤ ለዚህም ስራ እንሰራለን። ጋዛን የእኛ ካደረግን በኋላ ያልፈነዱ አደገኛ ቦምቦችንና ሌሎች መሳሪያዎችን እናከሽፋለን፣ የፈራረሰውን ቦታ አስተካክለን ብዙ የስራ ዕድል እንፈጥራለን፤ በአካባቢው ላሉ ሰዎች መኖሪያ የሚሆን ቤት በመገንባት ኢኮኖሚያዊ ልማት እናካሂዳለን" ብለዋል።
ትራምፕ አክለውም ሌሎች ጎረቤት ሀገራት የተፈናቀሉ ጋዛውያንን እንዲወሰዷቸው ጠይቀዋል።
ከባለፈው ጥር ወር መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ ፕሬዝደንት ትራምፕ ግብጽና ጆርዳን ይህን እንዲያደርጉ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል። ግብጽና ጆርዳንና ሌሎች የአረብ ሀገራት ትራምፕ ያቀረቡትን ሀሳብ በጽኑ ተቃውመውታል።
ትራምፕ 1.8 ሚሊዮን ለሚሆኑ ፍልስጤማውያን ማረፊያ የሚሆን ቦታ ማዘጋጀት የሚፈልጉ ሀገራት መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
የአሜሪካ ወታደሮችን ወደ ጋዛ ለመላክ አስበው እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ "አስፈላጊ የሆነውን እናደርጋለን፤ አስፈላጊ ከሆነ እናደርገዋለን።መሬቱን ወስደን በሺዎች የሚቆጠሩ ስራ በመፍጠር አጠቃላይ መካከለኛው ምስራቅ የሚኮራበት ስራ እንሰራለን" ሲሉ መልሰዋል።
አሜሪካ የእስራኤልና ፍልስጤምን ሁለት ሀገርነት መፍትሄ ወይም 'ቱ ስቴት ሶሉሽንን' ለበርካታ አስርት አመታት ስትደግፍ ቆይታለች። ትራምፕ አሜሪካ ይህን ፖሊሲዋን ቀይራ እንደሆነ ተጠይቀው "ከሁለት ሀገርነት ወይም ከሌላ ጋር አይገናኝም...ህዝብ የተሻለ ኑሮ እንዲኖር እንፈልጋለን፣ ምክንያቱም የጋዛ ሰርጥ ወደ ገሀነምነት ተቀይሯል" ሲሉ መልሰዋል።
እስራኤልና ሀማስ በግብጽና ኳታር አደራዳሪነት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው መጠነሰፊ ጥቃት ከ47ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።
ሀማስ ጥቅምት 7፣2023 በደቡብ እስራኤል ድንበር ጥሶ በመግባት 1200 ሰዎችን ከደገለ እና 250 ሰዎችን አግቶ መወሰዱን ተከትሎ ነበር ሀሰማስና እስራኤል ወደ አጠቃላይ ጦርነት የጠቡት።