ሀገራቸውን ከነጻነቷ በፊት ጀምሮ ጠ/ሚ ሆነው ያገለገሉት ልዑሉ ለረዥም ጊዜ ካገለገሉ የዓለም መሪዎች አንዱ ናቸው
የባህሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ልዑል ከሊፋ ቢን ሰልማን ዓረፉ
የባህሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ልዑል ከሊፋ ቢን ሰልማን በ84 ዓመታቸው ማረፋቸውን ንጉሳዊው ቤተ-መንግስት ዛሬ ረቡዕ ህዳር 02 ቀን 2013 ዓ.ም አስታወቀ ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት የሳምንት የሀዘን ጊዜ የታወጀ ሲሆን መንግስት የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ እንዲሁም ከነገ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የመንግስት መስሪያ ቤቶች እንዲዘጉ ወስኗል፡፡
የባህሬን የዜና ወኪል “ንጉሳዊው ፍርድ ቤት ዛሬ ጠዋት በአሜሪካ ማዮ ክሊኒክ ህይወታቸውን ባጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ልዑል ከሊፋ ቢን ሳልማን ሞት ሀዘኑን ገልጿል” ሲል ዘግቧል
አስከሬኑ ከአሜሪካ ከተመለሰ በኋላ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ የተወሰኑ ዘመዶቻቸው ብቻ በተገኙበት ይከናወናል ነው የተባለው፡፡
ልዑል ከሊፋ ባህሬን ነጻ ከመውጣቷ ከአንድ ዓመት በፊት ፣ ማለትም እ.ኤ.አ. ከ1970 ጀምሮ ሀገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡
ልዑሉ ህክምና ሲያደርጉበት የነበረው የአሜሪካው ማዮ ከሊኒክ በቅርቡ ያረፉት የኩዌት አሚር ሼክ ሳባህን ጨምሮ ከፍተኛ የባህረ ሰላጤው ባለስልጣናትን በማከም የረዥም ጊዜ ልምድ ያለው ነው፡፡
በአውሮፓውያኑ 2004 ፣ የዩኤኢ መስራች አባት በመባል የሚታወቁት ሼክ ዛይድ ክሊኒኩ የልብ ህክምና ማዕከል እንዲያቋቁም 25 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርገዋል፡፡