ዩኤኢ እና ባህሬን ከእስራኤል ጋር ታሪካዊውን የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ
እስራኤል ከአረብ ሀገር ጋር የሰላም ስምምነት ስትፈራረም ከ26 ዓመታት በኋላ የአሁኑ የመጀመሪያዋ ነው
የሰላም ስምምነቱ “ለመካከለኛው ምስራቅ አዲስ ጎህ እንደሚቀድ” ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናግረዋል
ዩኤኢ እና ባህሬን ከእስራኤል ጋር ታሪካዊውንየሰላም ስምምነት በዋይት ሀውስ ተፈራረሙ
በፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅት እና እስራኤል መካከል እ.ኤ.አ. በ 1993 የኦስሎ ስምምነት ከተፈረመ ከ 26 ዓመታት በላይ ከዘለቀ ቖይታ በኋላ ዛሬ በዋይት ሃውስ በእስራኤል እና በአረብ ሀገራት መካከል የመጀመሪያው የሰላም ስምምነት ተፈርሟል፡፡
በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ እስራኤል ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ከባህሬን ጋር ስምምነት እንድትደርስ አሜሪካ የማደራደሩን ስራ አከናውናለች፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የባህሬን መንግሥት በፊርማው ሥነ-ስርዓት ላይ በቅደም ተከተል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን እና አብዱል ላቲፍ ቢን ራሺድ አል ዛያኒ የተወከሉ ሲሆኑ እስራኤል ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተወክላለች፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የስምምነቱ መፈረም “ለመካከለኛው ምስራቅ አዲስ ጎህ እንደሚቀድ” በመግለጽ ታሪካዊውን የአብርሃም ስምምነት ሥነ-ስርዓት ከፍተዋል፡፡
የእነዚህ ሶስት ሀገራት መሪዎች “ላሳዩት ታላቅ ድፍረት ምስጋና ይግባቸዋል” ያሉት ትራምፕ “ማንኛውም እምነት እና ታሪክ ያላቸው ሰዎች በሰላም እና በብልፅግና አብረው የሚኖሩበትን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ትልቅ እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“እነዚህ ስምምነቶች በመላ አካባቢያችን ሁሉን አቀፍ ሰላም እንዲሰፍን መሠረት ሆነው ያገለግላሉ ፤ ይህ ሊሆን ይችላል ብሎ ማንም አላሰበውም”ም ብለዋል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኒታኒያሁ ”እስረኤል 1,000 ዓመታት ያህል ስለሰላም ስትጸልይ ነበር” ያሉ ሲሆን ዛሬ ለተደረሰው የተሳካ ስምምነት ፕሬዘዳንት ትራምፕን አመስግነዋል፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ የማይታመን የሚመስል የሰላም ስምምት መደረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
“የእስራኤል ሰው ጦርነትን ያውቀዋል፤ እኔም አውቀዋለሁ፡፡ ከጎኔ የነበረ ታጋይ ህይወቱን እጄ ላይ አጥቷል፡፡ ወንድሜ በጦርነት ነው የሞተዋው:: የጦርነትን ዋጋ አውቀዋለሁ” ብለዋል፡፡
“የሰላም ስጦታው ከባድ ነው” ያሉት ኔታኒያሁ ይህ ስምምነት ወደ ሌሎች የአረብ ሀገራት ተዛምቶ የአረብና እራኤል ግጭት እስከመበረሻው እዲቆም ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ስምምነቱ ከሰላም ባሻገር በመካከለኛ ምስራቅ የኢኮኖሚ ትብብር ያመጣል፡፡
“ቀኑ የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና የግንኙነት ታሪክ መቀየሩን የምንመሰክርበት ነው” ያሉት የዩኤኢ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን ስምምነቱ ትልቅ ተስፋን በቀጣናውና በመላው ዓለም የሚፈነጥቅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ለስምምነቱ መሳካት ጉልህ ሚና የተጫወቱ አካላትን ያመሰገኑም ሲሆን “ሰብዓዊ እንግልትና ስቃዮችን የሚያስቀር የቀጣናውን የወደፊት የመልማትና የማደግ ፍላጎት ለማሳካት የሚያስችልም ነው” ብለዋል፡፡
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በትልቅ ቁርጠኝነት የተፈረመው ስምምነት የፍልስጤምን ጥያቄዎች አመክንዮአዊ በሆነ መንገድ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡
ከሳምንታት በፊት የተደረሰው ስምምነት እስራኤል አንዳንድ የፍልስጤም ግዛቶችን ወደ ራሷ ለማካተት የጀመረችውን ጥረት እንድታቋርጥ የሚያስችል ነው መባሉ የሚታወስ ነው፡፡
የባህሬይኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱላቲፍ አል ዛያኒ በበኩላቸው ቀኑ ለመካከለኛው እውነተኛው ታሪካዊ ቀን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ለቀጣናው የወደፊት ብሩህነት ትልቅ አበርክቶ አለው ያሉም ሲሆን ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ ከፍ ያለ ዋጋ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
ከባህሬይን ህዝብና ንጉሳዊ ቤተሰቦች ድጋፍ ያገኘው ስምምነቱ ህዝብ የሚገባውን ዘላቂ ሰላም እንዲያገኝ ለማድረግ እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት፡፡