የባልቲሞር ድልድይ መደርመስ በአሜሪካ ላይ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ምን ያህል ነው?
የአሜሪካ የባልቲሞር ረጅም ድልድይ በመርከብ ተገጭቶ መደርመሱ ይታወሳል
የባልቲሞር ወደብ መዘጋት የአሜሪካ ኢኮኖሚን በቀን እስከ 15 ሚሊዮን ዶላር ያሳጣል ተብሏል
የአሜሪካ የወደብ ከተማዋ ባልቲሞር ረጅም ድልድይ ባሳለፍነው ረቡዕ በእቃ ጫኝ መርከብ ተገጭቶ መደርመሱ ይታወሳል።
2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ድልድይ ተደርምሶ ወደ ፓታፕስኮ ወንዝ ውስጥ የገባ ሲሆን፤ በወቅቱም ከ20 በላይ ሰዎችና በርካታ ተሽርካሪዎችም ወደ ወንዙ መግባታቸው ተገልጿል።
አደጋውን ተከትሎ በተሰራው የነፍስ አድን ስራ የበርካቶች ህይወት መታደግ ቢቻልም ስድስት ሰዎች አሁንም ደብዛቸው እንደጠፋ ነው የተባለ ሲሆን፤ የጠፉት ሰዎች ሞተዋል ወደሚል ድምዳሜ እየተደረሰ መሆኑም ነው የተገለጸው።
አደጋውን ተከትሎም በዚያ መርመስ የሚደረጉ የመርከብ እንቅስቀሴዎች መወቆማቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ሆኖም ግን ወደቡ እንዳልተዘጋ እና አሁንም ስራ ላይ መሆኑነው የተገለጸው።
ትልቁ የባልቲሞር ድልድይ መደርመሱም በአሜሪካ በጣም እነቅስቀሴ ከሚበዛባቸው ወደቦች አንዱ በሆነው በባልቲሞር ወደብ ላይ ያለው የመርከብ ትራፊክ ላተወሰነ ጊዜ እንዲቆም አድርጓል።
ሜሪላንድ የድልድዩን ፍርስራሽ ለማሳትና ባህሩን ለማጽዳት ከአሜሪካ የፌደራል መንግስት 60 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እንደምትቀብልም ነው የተገለጸው።
የባልቲሞር ወደብ ለንግድ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
የባልቲሞር ወደብ በአጠቃላይ የንግድ እንቅስቀሴ መጠን ዘጠነኛ ትልቁ የአሜሪካ ወደብ ነው። ወደቡ መኪናዎችን፣ ማሽነሪዎችን፣ የእርሻ መሳሪያዎችን፣ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ እና ስኳርን ጨምሮ በርካታ ጭነቶችን ያስተናግዳል።
በፈረንጆቹ 2023 ብቻ 50 ሚሊዮን ቶን ጭነት እና 80 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ጭነት በባልቲሞር ወደብ በኩል በአሜሪካ እና በሌሎች ሀገሮች መካከል መንቀሳቀሱም ተነግሯል።
የሜሪላንድ ስቴት መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ በባልቲሞር ወደብ በኩል 847 ሺህ 158 አውቶሞቢሎች ጭነት አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 70 በመቶ አውቶሞቢሎች ወደ አሜሪካ የገቡ ናቸው።
ወደ 20 በመቶ የሚጠጋው የአሜሪካ የድንጋይ ከሰል ወደ ውጭ የሚላከው በባልቲሞር ወደብ በኩል ነው።
የድልድዩ መፍረስ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ምን ያህል ነው?
የአሜሪካ ፌደራል መንግስት የሜሪላንድ ተወካይ ዴቪድ ትሮን ድልድዩ በፈረሰበት ወቅት በስፍራው ተገኝተው በሰጡት መግለጫ፤ የወደቡ መዘጋት የአሜሪካ ኢኮኖሚ በቀን 15 ሚሊየን ዶላር እድሚያሳጣ ገምተዋል።
በተጨማሪም ወደቡ ከ15 ሸህ በላይ ሰዎች በቀጥታ የስራ እድል የፈጠረ እና 140 ሺህ ሰዎች ደግሞ በአጠቃላይ የወደብ እንቅስቃሴ ላይ በበመስረት የስራ እድል ያገኙ መሆናቸውን የሜሪላንድ ገዥ ዌስ ሙር ተናግረዋል።
ይህ ማለት የወደቡ መዘጋት ሰራተኞችን ከስራ የሚያስባርር ባይሆንም፤ ዝቅተኛ እንቅስቃሴ በሚኖርበት ወቅት ዝቅተኛ ስራ ይኖራል፤ ከዚህ አንጻ ደግሞ በቀን ስራ የሚተዳደሩ ሰዎች ገቢያቸው በእጅጉ እንዲቀንስ ያደርጋል ብለዋል።
በድልድዩ ላይ የደረሰውን ጉዳት ጨምሮ በተሸከርካሪዎች እና በሰዎች ላይ ከደረሰው ጉዳት ጋር ተያይዞም የኢንሹራንስ ኩበንያዎችም እስከ 3 ቢሊየን ዶላር ካሳ ክፍያ ሊጠየቁ እንደሚችሉም ብሎምበርግ አስነብቧል።