አሜሪካ ተመቱ ስለታበሉት መርከቦች እስካሁን ያለችው ነገር የለም
የአሜሪካ ሁለት መርከቦች በየመን አማጺያን መመታታቸው ተገለጸ፡፡
ከስድስት ወር በፊት ለፍልስጤማዊያን ነጻነት እታገላለሁ የሚለው ሐማስ በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት አሁንም መቋጫ አላገኘም፡፡
ለ30 ሺህ ፍልስጤማዊያን ግድያ ምክንያት በሆነው በዚሕ ጦርነት የሚሳተፉ አካላት ቀስ በቀስ እየሰፉ እና ጉዳቱም እየጨመረ የመጣ ሲሆን የየመን ሁቲ አማጺያን ዋነኞቹ ናቸው፡፡
አሜሪካ እስራኤል ከመደገፍ እንድትታቀብ እና እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ጥቃት እንድታቆም ጫና ለመፍጠር የተጀመረው የሁቲ አማጺ ቡድን ጥቃት እንዲቆም አሜሪካ እና አውሮፓ የባህር ሀይላቸውን ወደ ቀይ ባህር ቢልኩም አማጺያኑ ግን አሁንም ጥቃታቸውን ገፍተውበታል፡፡
የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር ጥቃት ሊያቆሙ የሚችሉት የእስራኤል ወረራ ከቆመ ብቻ ነው አሉ
የአማጺያኑን ጥቃት ለማስቆም እና የቀይ ባህር ትራንስፖርትን ደህንነት ለማረጋገጥ ወደ ስፍራው ከመጡት የአሜሪካ የጦር መርከቦች ሁለቱ መጠቃታቸው ተገልጿል፡፡
ሮይተርስ የአማጺ ቡድኑን ቃል አቀባይ ያህያ ሳርዓን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ የአሜሪካ ሁለት የጦር መርከቦች ከባህር ላይ በሚተኮስ ሚሳኤል እና ድሮኖች አማካኝነት ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡
ይሁንና አሜሪካ እስካሁን በቀይ ባህር ተመቱ ስለተባሉት መርከቦቿ ያወጣችው መረጃ እንደሌለ ተገልጿል፡፡
35 በመቶ የሚሆነው የዓለም ንግድ የሚሳለጥበት ቀይ ባህር በእስራኤል ሐማስ ጦርነት ምክንያት የተቀዛቀዘ ሲሆን የንግድ መርከቦች ረጅም እና ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙ ከማስገደዱ ባለፈ ዓለም ትራንስፖርት እና መድህን ዋጋ እንዲጨምርም አድርጓል፡፡
ግብጽ ከስዊዝ ካናል ስታገኘው የነበረው ገቢ በግማሽ እንደቀነሰባት ስትገልጽ በወር እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እያጣች መሆኗን አስታውቃለች፡፡