የባልቲሞር ድልድይ ተደርምሶ ወንዝ ውስጥ ገባ
በአደጋው ምክንያት ከ20 በላይ ሰዎች እና በርካታ ተሽከርካሪዎች ወደ ወንዝ መግባታቸው ተገልጿል
ረጅሙ ድልድይ የተደረመሰው እቃ በጫነች መርከብ ተገጭቶ ነው ተብሏል
የአሜሪካ የወደብ ከተማዋ ባልቲሞር ረጅም ድልድይ ተደረመሰ።
2 ነጥብ 5 ኪሎሜትር የሚረዝመው ድልድይ ተደርምሶ ወደ ፓታፕስኮ ወንዝ ሲገባ የሚያሳዩ ምስሎችም ወጥተዋል።
ድልድዩ የተደረመሰው በመርከብ ተገጭቶ ነው የተባለ ሲሆን፥ ከ20 በላይ ሰዎችና በርካታ ተሽርካሪዎችም ወደ ወንዙ መግባታቸው ተገልጿል።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችም ወንዝ ውስጥ የገቡትን ሰዎች ለማውጣት እየተረባረቡ መሆኑን የባልቲሞር ፖሊስን ጠቅሶ ሬውተርስ ዘግቧል።
የባልቲሞር ፖሊስ አዛዥ ጀምስ ዋልስ ከወንዙ አራት ሰዎችን ማውጣት መቻሉና የሁለቱ ህይወት አስጊ በመሆኑ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል ብለዋል።
የሜሊርላንድ አስተዳዳሪ ዌስ ሞር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁ ሲሆን፥ የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ)ም በስፍራው እንደሚገኝ አስታውቋል።
ኤፍቢአይ እስካሁን ባደረገው ምርመራ አደጋው ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ መጠቀሱን ቢቢሲ ዘግቧል።
የባልቲሞር ወደብ በአሜሪካ ስራ ከሚበዛባቸው ወደቦች ቀዳሚው ነው፤ በ2022 ብቻ ከ750 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን ጭነት ማስተናገዱም ተገልጿል።
ድልድዩ ከመደርመሱ በፊት
ከባልቲሞር ድልድይ ጋር የተጋጨችው በሆላንዱ ማርስክ ኩባንያ የምትተዳደር መርከብ የደረሰባት ጉዳትና ወደቡ ስራ ስለማቋረጡ ግን እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
የማሪን ትራፊክ ድረገጽ መረጃ እንደሚያሳየው ከአደጋው መከሰት በኋላ ከ40 በላይ አነስተኛ የጭነት መርከቦች በባልቲሞር ወደብ ቆመዋል፤ በጥቂቱ 30 መርከቦችም ወደ ወደቡ እየተጓዙ ነበር።
“ፍራንሲስ ስኮት ኪ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የባልቲሞር ድልድይ በፈረንጆቹ 1977 ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የሬውተስ ዘገባ አውስቷል።