የበለጸጉ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ “ቃል የገቡትን የ100 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ድጋፍ” አለመፈጸማቸው ተቀባይነት የለውም- አፍሪካ ህብረት
አፍሪካ በየዓመቱ ለምግብ ግዢ 45 ቢሊዮን ዶላር ታወጣለች ተባለ
የአፍሪካ ሀገራት ለጥቅማቸው የጋር አቋማቸውን ለማንጸባረቅ እየሰሩ ናቸው ብሏል ህብረቱ
የበለጸጉ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ “ቃል የገቡትን የ100 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ድጋፍ” አለመፈጸማቸው ተቀባይነት እንደሌለው በአፍሪካ ህብረት የግብርና ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ ገለጹ፡፡
ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ በአፍሪካ የምግብ ስርዓት ዙሪያ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ አፍሪካ በምግብ ራሷን ለማቻል በምታደርገው ጥረት “የአየር ንብረት ለውጥ” ዋነኛ ፈተና መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ እንደፈረንጆቹ 2015 በፈረንሳይ በተካሄደውና የፓሪስ ስምምነት ተብሎ የሚታወቀው 21ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የበለጸጉ ሀገራት እያደጉ ላሉ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን እንዲቋቋሙ የ100 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ቢገቡም ገንዘቡን እየሰጡ እንዳልሆነ ተናግሯል፡፡
የበለጸጉት ሀገራት በሚለቁት በካይ ጋዝ ዋነኛ ተጎጂ የሆኑት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት መሆናቸውን ያነሱት ኮሚሽነሯ የገቡትን ቃል አለመፈጸማቸው ተቀባይነት የለውም ብሏል።
በመሆኑም የበለጸጉ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ የፋይናንስ ድጋፉን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጪው ህዳር 2021በስኮትላንድ ግላስኮው የሚካሄደው 26ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ መሰጠት አለበት”ም ነው ያሉት አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ።
የአፍሪካ ሀገራት በአፍሪካ ህብረት በኩል በጉባኤው ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥና ድምጻቸው እንዲሰማ በጋራ አቋማቸውን ለማንጸባረቅ መዘጋጀታቸውንም አስታውቋል።
በሌላ በኩል አፍሪካውያን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ምርታማነታቸውን በእጥፍ ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው ኮሚሽነሯ ተናግሯል፡፡
የአፍሪካ ሀገራት 60 በመቶ የሚታረስ መሬት ይዘው “በየዓመቱ ለምግብ ግዢ 45 ቢሊዮን ዶላር ያወጣሉ” ያሉት ኮሚሽነሯ፤ ይህን ታሪክ መቀየር ከቻሉ እና ያላቸውን እምቅ አቅም ከተጠቀሙ ለአፍሪካ አይደለም ለዓለም የሚተርፍ አቅም እንዳለም ተገልጿል፡፡
ኮሚሽነሯ አፍሪካውያን “ለግብርና የሚያወጡትን ዓመታዊ የገንዘብ መጠን ማሳደግ፣ እምቅ የግብርና ምርት ያለባቸውን አካባቢዎች በክላስተር በመለየት ምርታማነትን ለማሳደግ መስራትና ምርት የሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂ የመጠቀም አቅማቸውን ማጎልበት እንደሚገባቸው”ም ጠቁመዋል።
አርሶ አደሮች በተለይም ሴት አርሶ አደሮች ለግብርና ፋይናንስ የሚያስፈልጋቸውን የብድር አቅርቦት ማመቻቸት እንደሚገባም ጭምር ተናግሯል።
“በአፍሪካ 50 በመቶ የሚሆኑት አርሶ አደሮች ሴቶች ናቸው”ያሉት ኮሚሽነሯ፤ ለሴቶች ድጋፍ ማድረግ በአፍሪካ የግብርና ምርማነትን ለማሳደግ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ብሏል።
የአፍሪካ ሀገራት የዜጎቻቸውን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መሆኑን ጠቁመው፤ “ይሄን በመገንዘብ ለጉዳዩ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይገባቸዋል”ም ነው ያሉት አምባሳደር ጆሴፋ።
የአፍሪካ ህብረት ለአባል አገራቱ የግብርና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ የገንዘብ፣ የቴክኒክና የፖሊሲ ማዕቀፍ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በ39ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ትናንት ከተወያየባቸው ጉዳዮች መካከል እንደፈረንጆቹ በ2022 የአፍሪካ ህብረት መሪ ሀሳብ “የተመጣጠነ ምግብና የምግብ ዋስትና” እንዲሆን በቀረበው ሀሳብ ላይ ውይይት ማድረጉን አስታውሰዋል።
ምክር ቤቱ ሀሳቡ ከዛሬ ጀምሮ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በበይነ መረብ በሚያደርጉት ሶስተኛው የአጋማሽ ዓመት የጥምር ውይይት ላይ እንደ አጀንዳ አድርጎ እንደሚያቀርብና በውይይቱ መሪ ሀሳቡን ያጸድቀዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል ኮሚሽነሯ።