የባርሴሎና ደጋፊዎች ዊሊያምስን ለማስፈረም በቲክ ቶክ ገንዘብ እያዋጡ ነው
የ22 አመቱ የአትሌቲክ ቢልባኦ የክንፍ ተጨዋች በአውሮፓ ክለቦች በቀዳሚነት ይፈለጋል
ዊሊያምስ ስፔን እንግሊዝን 2-1 ባሸነፈችበት ጨዋታ ላይ አንድ ግብ አስቆጥሯል
የባርሴሎና ደጋፊዎች ዊሊያምስን ለማስፈረም በቲክ ቶክ ገንዘብ እያዋጡ ነው።
የባርሴሎና ደጋፊዎች የላሊጋው ክለብ አጥቂውን ኢኮ ዊሊያምስን እንዲያስፈርምላቸው በክለቡ ይፋዊ የቲክ ቶክ አካውንት ላይ የገንዘብ አስተዋጽኦ እያደረጉ ናቸው።
የ22 አመቱ የአትሌቲክ ቢልባኦ የክንፍ ተጨዋች፣ ስፔን የአውሮፓ ዋንጫን ለማሸነፍ ባደረገችው የሰባት ወራት ጉዞ የተዋጣላቸው ከሚባሉት ተጨዋቾች ውስጥ አንዱ በመሆኑ የአውሮፓ ክለቦች በቀዳሚነት ይፈልጉታል።
ስፔን እንግሊዚን 2-1 ባሸነፈችበት የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ የመክፈቻዋን ግብ ያስቆጠረው ዊሊያምስ፣ በውድድሩ ምርጥ ከተባለው ላሚን ያማል ጋር ያሳየው ጥምረት ተስፋ ተጥሎበታል።
በቅርቡ የገንዘብ እጥረት ለገጠመው የካታላኑ ክለብ ገንዘብ እያዋጡ ያሉት ደጋፋዎችም ያማል እና ዊሊያምስ በጥምረት ሆነው ሲያጠቁ ማየት ይፈልጋሉ።
"ኒኮን አስፈርሙ"፣ "ኒኮን መቶ በመቶ እንፈልገዋለን"፣ "ለኒኮ ዊሊያምስ" የሚሉት ባርሴሎና በቅርቡ በለቀቃቸው የቲክ ቶክ ቪዲዮች ስር ከለቀቁት አስተያየቶች ውስጥ የተወሰኑት ናቸው።
የትራንስፈር መረጃ እንደሚያሳየው አሁን ላይ የዊሊያምስ ወቅታዊ ዋጋ 70 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን የስፔን ሚዲያዎች ግን አትሌቲክ ዊሊያምስን በ58 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚሸጠው ዘግበዋል።
የባርሴሎና ደጋፊዎች "ሸልማት" በሚል በቲክ ቶክ ያዋጡት ከ5 ሳንቲም እስከ 1 ዩሮ በመሆኑ ምኞታቸውን ለመግለጽ እንጂ ለክለብ ብዙ የሚባል ድጋፍ አይደለም።
በላሊጋ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው እና በሻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ በሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ግስጋሴው ተገታው ባርሴሎና በክረምቱ የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት እስካሁን ምንም ተጨዋች አላስፈረመም።