የሽብር ጥቃት ስጋት ያንዣበበበት የፒኤስጂ እና ባርሴሎና የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ
የፈረንሳይ ፖሊስ በፓሪስ በርካታ የጸጥታ ሃይሎችን በማሰማራት ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ ነው ተብሏል
አይኤስ በ2015 በፓርክ ደ ፕሪንስ የሽብር ጥቃት ለማድረስ መሞከሩ ይታወሳል
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽትም ቀጥለው ይካሄዳሉ።
ፒኤስጂ በፓርክ ደ ፕሪንስ የስፔኑን ባርሴሎና፤ አትሌቲኮ ማድሪድ ደግሞ የጀርመኑን ዶርትሙንድ በሜትሮፕፖሊታኖ ስታዲየም ምሽት 4 ስአት ያስተናግዳሉ።
ተጠባቂዎቹ ጨዋታዎች የሽብር ጥቃት ኢላማ ናቸው የሚሉ ዘገባዎች ከወጡ በኋላ የፈረንሳይና ስፔን የጸጥታ ተቋማት ጥበቃቸውን ማጠናከራቸው ተገልጿል።
አይኤስ ደጋፊዎቹ የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያዎች በሚካሄዱባቸው ስታዲየሞች የሽብር ጥቃት እንዲፈጽሙ ማዘዙን ተከትሎ ነው ሀገራቱ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በጥብቅ እየተከታተሉ ነው የተባለው።
የፈረንሳይ ፖሊስ በፓርክ ደ ፕሪንስ ዙሪያ ተሽከርካሪዎችን ማቆም ከልክሎ ፍተሻውን ማጠናከሩን ሬውተርስ ዘግቧል።
የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር የሽብር ቡድኑ የጥቃት ዛቻ በተመለከተ መረጃ እንደደረሰውና ጨዋታዎቹ በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት እንደሚካሄዱ ማስታወቁ ይታወሳል።
በትናንናው እለት የተደረጉት የአርሰናል እና ባየር ሙኒክ እንዲሁም የሪያል ማድሪድ እና ማንቸስተር ሲቲ ጨዋታዎች ያለምንም የጸጥታ ችግር መጠናቀቃቸውም አይዘነጋም።
ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት የተፈጸመባት ፈረንሳይ ግን የአይኤስን የሽብር ጥቃት ዛቻ በቀላሉ አትመለከተውም ነው የተባለው።
የአይኤስ ሶስት አጥፍት ጠፊዎች በ2015 ፈረንሳይ በፓርክ ደ ፕሪንስ ከጀርመን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ስታደርግ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሙከራ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ቡድኑ የ2015ቱን የጥቃት ሙከራ ምስል በማያያዝ ዘንድሮም እንዲደገም “ሁሉንም ግደሏቸው” ከሚል ጽሁፍ ጋር አል አዛይም ፋውንዴሽን በተሰኘ የሚዲያ ተቋሙ ማውጣቱ ተገልጿል።
በቀጣይ ሀምሌ ወር ኦሎምፒክ የምታስተናግደው ፓሪስ ስጋቱን የሚመጥን ቅድመ ዝግጅት ማድረጓን የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ጀራልድ ዳርማኒን በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል።
የፒኤስጂ ደጋፊዎችም የሽብር ቡድኑ ያስተላለፈው መልዕክት ክለባቸውን ለመደገፍ ስታዲየም ከመግባት እንደማያግዳቸው ተናግረዋል።
ማቲው የተባለ ደጋፊ “አልፈራም፤ በፍርሃት መኖር አንችልም፤ ስታዲየም ገብተን ምንም እንደማይፈጠር እናሳያቸዋለን” ማለቱንም ፍራንስ 24 ዘግቧል።
በተያያዘ ስፔንም ከ2 ሺህ በላይ የጸጥታ ሃይሎችን በማሰማራት የምሽቱ የአትሌቲኮ ማድሪድ እና ዶርትሙንድ ጨዋታ በሰላም እንዲጠናቀቅ እየተጋች ነው ተብሏል።