ጋርዲዮላን ከባርሴሎና ሶስትዮሽ ግስጋሴ ያስቆመው ኢንተር ሚላን ዘንድሮስ ይሳካለት ይሆን?
ማንቸስተር ሲቲ የመጀመሪያውን የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ለማንሳት ዛሬ ከጣሊያኑ ኢንተር ሚላን ጋር በቱርክ ኢስታንቡል ይፋለማል
ኢንተር ሶስት ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫውን አንስቷል
የቱርኩ አታቱርክ ኦሎምፒክ ስታዲየም ዛሬ ምሽት 4 ስአት ተጠባቂውን የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ያስተናግዳል።
የፕሪሚየር ሊግ እና ኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫዎችን ያነሳው ማንቸስተር ሲቲ ሻምፒዮንስ ሊጉን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳትና ለሶስትዮሽ ክብር ይጫወታል።
በሻምፒዮንስ ሊጉ በሶስት አመት ለሁለተኛ ጊዜ ለፍጻሜ የደረሰው የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን በ2020/21 በቼልሲ ተሸንፎ ዋንጫውን ማጣቱ ይታወሳል።
ዛሬ በኢስታንቡል ከኢንተር ሚላን ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ በድል በመደምደም ትልቁን የአውሮፓ ዋንጫ ለማንሳት መዘጋጀታቸውን ወሳኙ የሲቲ ተጫዋች ኬቨን ደብሩይነ ተናግሯል።
ሲቲ ዋንጫውን የሚያነሳ ከሆነ በ1998/99 የውድድር አመት የሻምፒዮንስ ሊግ፣ ፕሪሚየር ሊግ እና ኤፍ ኤ ካፕ በማንሳት ሶስትዮሽ ካሳካው ማንቸስተር ዩናይትድ በመቀጠል ሁለተኛው የእንግሊዝ ክለብ ይሆናል።
ባለፉት 26 ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ የተሸነፈው የጋርዲዮላ ቡድን በአውሮፓ መድረክ አንድም ሽንፈት አላስተናገደም፤ ከ12 ጨዋታዎች በሰባቱ አሸንፎ በሌሎቹ ነጥብ ተጋርቷል።
ጋርዲዮላ በ2011 ከባርሴሎና ጋር ካነሱት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ በኋላ ከሲቲ ጋር የመጀመሪያውን የአውሮፓ ትልቁን ዋንጫ ለመሳም በወረቀት ደረጃ የበላይነት አላቸው።
ጋርዲዮላ ስለስኬታማው አመታቸው ተጠይቀው፥ “ከዚህ ቀደም ሜሲን የመሰለ ኮከብ ተጫዋች ነበረኝ፤ አሁን ደግሞ ሃላንድ፤ እየቀለድኩ አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በእንግሊዝ ሪከርዶችን የሰባበረው ኧርሊንግ ሃላንድ በአታቱርክ ስታዲየም ተአምር እንዲያሳይ ደጋፊዎቹ ይጠብቃሉ።
አራተኛ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫውን ለመውሰድ የሚታገለው የጣሊያኑ ክለብ ኢንተር ሚላን ለሲቲ በቀላሉ እጅ ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም።
በሻምፒዮንስ ሊጉ ከ12 ፍልሚያዎች በስምንቱ ያሸነፈው ኢንተር ሚላን በሴሪአው ሶስተኛ ሆኖ ቢያጠናቅቅም የኮፓ ኢታሊያ ዋንቻን ለሁለት ተከታታይ አመት አንስቷል።
የሲሞኒ ኢንዛጊ ቡድን በላውታሩ ማርቲኔዝ፣ ኤዲን ዤኮ እና ሮሜሉ ሉካኩ ጠንካራ የፊት መስመር እየተመራ የሲቲን ተከላካይ መስመር እንደሚፈትን ይጠበቃል።
ኢንተር በፈረንጆቹ 2010 በጆዜ ሞሪንሆ እየተመራ9 የጋርዲዮላውን ባርሴሎና ከሻምፒዮንስ ሊጉ የግማሽ ፍጻሜ ውጭ ማድረጉ ይታወሳል።