የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ተወደድብን ያሉ የስፔኗ ባርሴሎና ነዋሪዎች ለተቃዎሙ አደባባይ ወጡ
“ግማሽ ደመወዛችንን ለኪራይ እያዋልን ነው” ያል ነዋሪዎች፤ የቤት ኪራይ ዋጋ ተመጣጣኝ እንዲሆን ጠይቀዋል
በባርሴሎና የዘንድሮ የቤት ኪራይ ዋጋ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጽ በ70 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል
የስፔኗ ባርሴሎና ከተማ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋ ተወዶብናል በማለት ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋል።
22 ሺህ የሚሆኑ የባርሴሎና ከተማ ነዋሪዎች በትናንትናው እለት በወጡት የተቃውሞ ሰልፍ፤ የመኖሪያ ቤት ዋጋ እንዲቀንስ እና የተሻለ የኑሮ ሁኔታ እንዲኖር ጠይቀዋል።
በስፔን የመኖሪያ ቤት በጣም አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ ነው የተባለ ሲሆን፤ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ሀገሪቱ ቱሪዝምን ለማሳደግ እየሰራች ባለበት ወቅት የቤት አከራዮች ቤታቸውን ከረጅም ጊዜ ይልቅ ለአጫጭር ቀናት ለሚመጡ ቱሪስቶች ማራየትን እየመረጡ መምጣታቸውን ተከትሎ ነው
በባርሴሎና በፈረንጆቹ 2024 ሁለተኛ ሩብ ዓመት የቤት ኪራይ ዋጋ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ70 ጭማሪ ማሳየቱን የካታላን ቤቶች ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል።
የተከራዮች ማህበር ቃል አቀባይ ካርኔ ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገረችው፤ “የገቢያችንን ግማሽ የቤት ኪራይ ላይ እያዋልን ነው፤ ይህ መቆም አለበት” ብላለች።
ከቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ ጋር በተያያዘ ከባርሴሎና በተጨማሪ በተለያዩ የካታሎኒያ ግዛቶች የተቃውሞ ሰልፎች መደረጋቸውም የተነገረ ሲሆን፤ ቡርጎስ፣ በሰሜን ስፔን አስቱሪያስ እና በደቡብ ጄሬዝ ዴ ላ ፍሮንቴራ ሰልፎች ተካሂደዋል።
የሀገሪቱ መንግስት ባሳለፍነው ሐምሌ ላይ ለበዓል በሚል የቤቶች ዋጋ ላይ መጠነኛ የዋጋ ቅናሽ መደጉን አስታውቆ እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ ግን የቤት ኪራይ ዋጋ በእጅጉ መጨመሩም ነው የተነገረው።
ከመኖሪያ ቤት ዋጋ ጋር በተያያዝ በያዝነው ዓመት ማድሪድ፣ በካናሪ ደሴቶች እና በማላጋ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን፤ እንደ መስተንግዶ ባሉ ዝቅተኛ ገቢ የሚያስገኙ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች ከመክፈል አቅም በተያያዘ ድንኳኖች እና መኪና ውስጥ ለማደር መገደዳቸውም ተነግሯል።