የኪራይ ቤት ዋጋ የናረባቸው የዓለማችን ከተሞች እነማን ናቸው?
ናይት ፍራንክ የተባለ ተቋም ባወጣው መረጃ ኒውዮርክ፣ ሲንጋፖርና ለንደን እስከ ሶስተኛ ያለውነ ደረጃ ይዘዋል
በ2022 የመጨረሻ ሩብ አመት በዓለማችን ከተሞች የመኖሪያ ቤቶች ኪራይ ዋጋ በአማካይ በ10 ነጥብ 2 በመቶ ጨምሯል
የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ በመላው አለም ባሉ ከተሞች ተባብሶ ቀጥሏል።
በተለይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ይዞት የመጣው የእንቅስቃሴ ገደብ መላላት ሲጀምር የኪራይ ዋጋው ማንሰራራቱ ነው የተነገረው።
በ2022 የመጨረሻ ሩብ አመት የታየው ጭማሪም የዚሁ ማሳያ ነው።
በአለማችን 10 ትልልቅ ከተሞች የዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ኪራይ በአማካይ በ10 ነጥብ 2 በመቶ መጨመሩን ነው ናይት ፍራንክ ግሎባል የተባለው የዘመናዊ ቤቶችን ኪራይ መረጃ የሚተነትን ተቋም ያስታወቀው።
የአሜሪካዋ ኒውዮርክ፣ ሲንጋፖርና ለንደን ከፍተኛ የኪራይ ዋጋን በማስመዝገብ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ያለውን ጣውደረጃ ይዘዋል።
ከአስሩ የአለማችን ግዙፍ ከተሞች የቤቶች ኪራይ ዋጋ ዝቅ ያለው በሁለት ከተሞች ብቻ ነው።
ሆንግ ኮንግ በኮቪድ 19 የእንቅስቃሴ ገደብ መላላት ፤ የኒውዝላንዷ ኦክላንድ በአቅርቦት መጨመር ምክንያት የኪራይ ዋጋ ቀንሶ ታይቶባቸዋል።
በ2022 ከፍተኛ ጭማሪ የታየባቸው አምስት ከተሞችም የሚከተሉት ናቸው።
የቤት ኪራይ የጨመረባቸው ከተሞች
1. ኒውዮርክ (31 በመቶ)
2. ሲንጋፖር - (22.9 በመቶ)
3. ለንደን - (19 በመቶ)
4. ቶሮንቶ - (14.5 በመቶ)
5. ሲድኒ - (8.9 በመቶ)
ከተሞች ከኮቪድ እቀባ በመውጣትና ጎብኝዎችን ለመሳብ አዳዲስ የቪዛ አማራጮችን ማስተዋወቃቸው የኪራይ ቤት ፍላጎቱን ማናሩ ተነግሯል።
በወረርሽኙ ምክንያት የጀመሩትን የቤት ግንባታ ማጠናቀቅ የተሳናቸውም አሁንም በኪራይ ቤቶች ህይወትን ለመግፋት መገደዳቸው አንዱ የዋጋ ንረቱ ምክንያት ተደርጎ ተነስቷል።
ጀኔቫ፣ ሞናኮ፣ ቶኪዬ፣ ኦክላንድ እና ሆንግ ኮንግ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።