የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ፀደቀ
አዋጁ በመኖሪያ ቤቶች ኪራይ ላይ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ በተቆጣጣሪ አካል እንዲወሰን የሚያደርግ ነው
አዋጁ ምክንያታዊ እና ፍትሃዊ ያልሆኑ የቤት ኪራይ ጭማሪዎች የሚያስቀር ነው ተብሎለታል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅን በዛሬው እለት አጸደቀ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ አጽድቋል።
በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ተስፋዬ በልጂጌ በሰጡት ማብራሪያ፤ መንገግስት የዜጎች መሰረታዊ ፍላጎት የሆነውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ለማሻሻል የተለያዩ ጥረቶች እየደረገ ቢሆንም፤ ከመኖሪያ ቤት ፍላጎት ጋር ሊጣጣም አልቻለም ሲሉ ተግናረዋል።
አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ አክለውም ፤ ምክንያታዊ እና ፍትሃዊ ያልሆኑ የቤት ኪራይ ጭማሪዎች በከተሞች እንደሚስተዋሉ አስገንዝበዋል።
የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ በተለይ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የከተማ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እያስነሳ እና ዜጎችም ተረጋግተው ኑሯቸውን እንዳይመሩ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይም በከተሞች አካባቢ የኑሮ ውድነትን ከሚያባብሱ ቁልፍ ችግሮች መካከል የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ አንዱ እንደሆነ መንግስት ይገነዘባል ብለዋል።
ለዚህም ይህንን ችግር ለመቅረፍ የመንግስት አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዋጁ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የአዋጁ ዋነኛ ዓላማ ግልጽ እና ተገማች የሆነ የመኖሪያ ቤት ኪራይ አስተዳደር እንዲሁም የአከራይ እና ተከራይ መብትን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የሚያስተናገድ ስርዓት መዘርጋ መሆኑን አብራርተዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትርጫልቱ ሳኒ አዋጁን በሚመለከት ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ ፤ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የመንግስት ሰራተኞችና የከተማ ነዋሪዎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ የተዘጋጀ አዋጅ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
ዜጎች ከሚያገኙት ገቢ ከ25 እስከ 30 በመቶ በላይ ለቤት ኪራይ ማዋል እንደማይጠበቅባቸው የገለጹት ወ/ሮ ጫልቱ፤ አንድ ተከራይ ለ2 ዓመት ያክል ያለምንም ጭማሪ በተከራየው ቤት ውስጥ ተረጋግቶ የመኖር መብት የሚሰጠው አዋጅ እንደሆነ አስረድተዋል።
የፍትህ ሚንስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በበኩላቸው አዋጁ በአከራዩ እና በተከራዩ መካከል አለመግባባት ካለ በተቆጣጣሪው አካል በሚደረግ አስተዳደራዊ ፍትህ የሚቀረፍ እንጂ በቀጥታ ጉዳዩ በፍድ ቤት እንደማይታይ ገልጸዋል።
አዋጁ የመኖሪያ ቤት ችግር በስፋት በሚስተዋልባቸው ከተሞች ተግባራዊ የሚደረግ ስለመሆኑና ዝርዝር አፈጻጸሙ ግን ለከተማ መስተዳድሮችና ለክልሎች እንደሚሰጥም ተገልጿል።
የምክር ቤቱ አባላት በአዋጁ ላይ በሰጡት አስተያየትም፤ አዋጁ በሀገሪቱ ከቤት ኪራይ ጋር ተያያዞ የሚስተዋሉ ፍትሃዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንደሚያስቀር እምነታቸውን ገልጸዋል።
እስካሁን የነበረው አካሄድ ስርዓት ያልነበረው እና የአከራይን መብት የበለጠ የሚደገፍ ነበር ያሉት የምክር ቤቱ አባል፤ አዲሱ አዋጅ የተከራይ እና አካራይ መብት ሚዛናዊ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት አከራዮች በፈለጉት ጊዜ ዋጋ ይጨምሩ ነበር፤ አሁን በጸደቀው አዋጅ ተቆጣጣሪ አካል በአመት አንድ ጊዜ በመንግስት በኩል የሀገሪቱን እና የኢኮኖሚዉን ነባራዊ ሁኔታ ታይቶ በመቶኛ በሚወስነው መሰረት የዋጋ ጭማሪ እንደሚደረግ ተደንግጓል።
አከራይ ለተከራይ ሊጠይቅ የሚገባው ክፍያ ከሁለት ወር ያለበለጠ እንዲሆን እንዲሁም አካራይ ተከራይ ቤቱን እንዲለቅ ሲፈልግ ሁለት ወር አስቀድሞ በጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ሊሰጠው እንደሚገባ በአዋጁ መደንገጉንም ተነግሯል።
የምክር ቤቱ አባላት በአዋጁ ላይ ከተወያዩ በኋላ መኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅን በሶስት ድምጸ ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።