በአዲስ አበባ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት የቤት ኪራይ ጭማሪ ማድረግ አይቻልም ተባለ
የኪራይ ጭማሪ አድርገው የሚገኙ አካላትን እንደሚጠይቅም ነው አስተዳደሩ ያስታወቀው
የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ “የቤት ኪራይ ጭማሪን ለ90 ቀናት ለማገድ የሚያስችል ደንብ” አጽድቋል
በአዲስ አበባ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት የቤት ኪራይ ጭማሪ ማድረግ ተከለከለ፡፡
የቤት ኪራይ ጭማሪን ለ90 ቀናት ለማገድ የሚያስችል ደንብ በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ መጽደቁን የአስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት አስታውቋል፡፡
ፕሬስ ሴክሬታሪያቱ ባወጣው መግለጫ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ የኑሮ ውድነት እየተባባሰ መሆኑን አንስቷል፡፡
የኑሮ ውድነቱ በአብዛኛው “አሳማኝ እና ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው በሰውሰራሽ ምክንያቶች የተፈጠረ ነው” ያለው መግለጫው የኑሮ ውድነቱ የከተማውን ነዋሪ ለከፍተኛ ችግር ዳርጓል ብሏል፡፡
“በሰሜን የሃገሪቱ ክፍል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የከተማችን ነዋሪ በገንዘብ መዋጮ፣ ለሠራዊት የሚሆን ስንቅ በማዘጋጀት፣ ደም በመለገስ እስከ ህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ባለበት በዚህ ወቅት፤ ጥቂት ስግብግብ ግለሰቦች አሁን ካለው ችግር ላይ አላግባብ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የተለያዩ ተግባራት ውስጥ ገብተው ይገኛሉ” ም ነው ፕሬስ ሴክሬታሪያቱ በመግለጫው ያለው፡፡
አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት በቤት ኪራይ ላይ ዋጋ ጭማሪ መታየቱንና ነዋሪዎች ቅሬታቸውን እያሰሙ መሆናቸውንም እንደ አብነት ያነሳው መግለጫው፤ የአስተዳደሩ ካቢኔ በቀን 18/12/13 ባደረገው መደበኛ ስብሰባው የነዋሪውን ቅሬታ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል ያለውን ደንብ ማጸደቁን አስታውቋል፡፡
“ደንቡ ከፀደቀበት ከ18/12/13 ዓ.ም ጀምሮ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መጨመርም ሆነ ተከራይን ከቤት ማስወጣት ለ90 ቀናት የተከለከለ ሲሆን በቀጣይም ታይቶ ክልከላው ለተጨማሪ ቀናት ሊራዘም ይችላል”ም ብሏል መግለጫው፡፡
ደንቡን በመተላለፍ ጭማሪ የተደረገበት ተከራይ አቤቱታውን በፅሑፍ ለወረዳው ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት በማቅረብ መፍትሄ እንዲያገኝ የሚቻልበት ሥርዓት በደንቡ መደንገጉንም ጭምር ነው መግለጫው የጠቆመው፡፡
በሚቀርቡ አቤቱታዎች ላይ ማጣራት ተደርጎ ጭማሪ ባደረገ አካል ላይ በደንቡ ተዘርዝሮ በተቀመጠው መሰረት ተጠያቂነት እንደሚኖርና እርምጃ እንደሚወሰድም ነው ተገልጿል፡፡