አይኤስ አይኤስ በኢራቅ ዳግም ማንሰራራቱ ተነገረ
አይ ኤስ አይ ኤስ በኢራቅ የነበረውን ይዞታ ከተነጠቀ ከሁለት አመታት በኋላ ዳግም አንሰራርቷል ተብሏል፡፡
የኩርድና የምዕራባውያኑ ጥምር የደህንነት ሀላፊዎች ለቢቢሲ እንደገለፁት ቡድኑ ከበፊቱ ይልቅ በመሳሪያ፣ በቴክኒክና በገንዘብ የተጠናከረ ሲሆን የሚሰነዝራቸው ጥቃቶችም ጨምረዋል ብለዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ታጣቂ ቡድኑ እንደ ቀድሞ ቦታ መቆጣጠር ሳይሆን የሚፈልገው አልቃይዳ ያደርግ እንደነበረው በኢራቅ ሀምሪን ተራራ ከመሬት በታች እየተደራጀ ነው ብለዋል፡፡
ቦታው ተራራማ መሆኑ ደግሞ የኢራቅ ጦር ታጣቂ ቡድኑን እንዳይቆጣጠር እንቅፋት ይሆንበታል ተብሏል፡፡በዋና ከተማዋ ባግዳድ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ደግሞ ቡድኑን ይበልጥ እንዳያጠናክረው ተሰግቷል፡፡
በስፍራው የሚገኙ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ጦር ኮማንደር እንደተናገሩት አሁን የተፈጠረው አይ ኤስ እራሱን ሰውሮ በምሽት ጥቃት ፈፅሞ የሚሸሽ ነው ብለዋል፡፡ ሀገሪቱ አሁን እየገጠማት ያለው ሁኔታ ለአካባቢውና ለሌሎች ሀገራት ስጋት መሆኑንም ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ