አደገኛ ዕፅ የማዘዋወር ወንጀል የፈፀመው ተከሳሽ በሰባት ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ
ደቡብ አፍሪካዊው ተከሳሽ ሄንደሪክ ክርስቲያን በፈፀመው የተከለከሉ አደገኛ የኮኬይን ዕጾች ማዘዋወር ወንጀል ተከሶ የእስራት እና የገንዘብ መቀጮ የፍርድ ውሳኔ ተላለፈበት፡፡
ተከሳሹ ጥቅምት 18 ቀን 2011 ዓ.ም በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ ከብራዚል ሳኦፖሎ በማድረግ ወደ ካሜሮን ያውንዴ ለመሄድ ለትራዚት ባረፈችበት ወቅት በተደረገ ፍተሻ ተይዞ ነበር፡፡
በዚህም እንዳይዘዋወር እና በጥቅም ላይ እንዳይውል የተከለከለውን 2 ሺህ 600 ግራም ኮኬይን የተባለ አደንዛዥ እጽ ይዞ በመገኘቱ ፍርድ ቤት መቅረቡን የክስ መዝገቡ ያስረዳል፡፡
የዐቃቤ ሕግ ክስ የተነበበለት ተከሳሽ የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ የወንጀል ድርጊቱን ፈፅሚያለሁ ጥፋተኛ ነኝ የገንዘብ እጥረት ስለገጠመኝ ነው በማለት ለችሎቱ ቃሉን ሰጥቷል፡፡
ዐቃቤ ሕግም ተከሳሽ ድርጊቱን ያመነ በመሆኑ የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዲሰጥ በማለት ለፍርድ ቤቱ ያመለከተ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን መርምሮ ተከሳሽ በተከሰሰበት ክስ ጥፋተኛ ተብሏል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 8ኛ ወንጀል ችሎት መዝገቡን መርምሮ ሪከርድ የሌለበትና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑን ማቅለያዎችን በመቀበል በ7 ዓመት ጽኑ እስራትና በ8 ሺህ 500 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ መወሰኑን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ አስታውቋል፡፡