ጭምብል ያላደረገችን ደንበኛ አላስተናግድም ያለው ባሬስታ የ80 ሺ ዶላር ጉርሻ አገኘ
ባሬስታው ጉርሻውን ያገኘው ተግባሩን ያደነቁ ብዙዎች በኦንላይን ባሰባሰቡለት ድጋፍ ነው
ያገኘውን ገንዘብ ዳንሰኛ የመሆን ህልሙን እውን ለማድረግ እንደሚገለገልበት ገልጿል
ጭምብል ያላደረገችን ደንበኛ አላስተናግድም ያለው ባሬስታ የ80 ሺ ዶላር ጉርሻ አገኘ
የፊትና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) ያላደረገችውን ደንበኛ አላስተናግድም ያለው የስታርባክስ ባሬስታ 80 ሺ ዶላር ገደማ ገንዘብን በጉርሻ (ቲፕ) መልክ ማግኘቱ ተሰምቷል፡፡
ሌኒን ጉቴሬዝ ይሰኛል የተባለው የ24 ዓመቱ ባሬስታ ጭምብሉን ካላደረገች ሊያስተናግዳት እንደማይችል በመግለጹ የደረሰበት ትችት ከፍተኛ ነው፡፡
በስፍራው የነበሩ ደንበኞችም የወጣቱን ድርጊት እና የሚያሳዩ ፎቶዎችን በማህበረሰብ የትስስር ገጾች ለጥፈው ጉዳዩ ለብዙዎች እንዲደርስና እንዲናኝ አድርገዋል፡፡
ይህም ነው ወጣቱ ሌኒን ጥቂት የማይባል ገንዘብን በጉርሻ መልክ እንዲያገኝ ያስቻለው፡፡
ጉዳዩን በማስመልከት ከሚሰጡ የአድናቆት አስተያየቶች ጋር በተያያዘ ‘ባገኘውና ጉርሻ በሰጠነው’ የሚሉ መልዕክቶች መብዛታቸውን የተመለከተውና ማት ኮዋን የተባለ የ26 ዓመት ወጣት “እንዲህ ከሆነ ለምን አንደግፈውም” በሚል የሚችሉና የሚፈቅዱ እንዲደግፉት የኦንላይን የድጋፍ ማሰባሰቢያ ዘመቻን (ጎ-ፈንድ ሚ) ከፍቷል፡፡
ኮዋን ይህን ሲያደርግ ከወጣቱ ባሬስታ ጋር አይተዋወቅም ነበረ፡፡
አንድ ሺ ዶላርን ለማሰባሰብ አቅዶ የጀመረው ዘመቻ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አገኘናም ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 80 ሺ ዶላር ገደማ ገንዘብን ለማሰባሰብ ቻለ፡፡
የተሰበሰበው ገንዘብ ከሌኒን እጅ እንዲደርስም ተደርጓል፡፡
ባሬስታው ሌኒንም ድጋፉን ያስተባበረለትን ወጣትና የደገፉትን ሁሉ አመስግኗል፡፡
ገንዘቡን ዳንሰኛ ለመሆን ያለውን ህልም እውን ለማድረግ እንደሚገለገልበትም ነው ለሲኤንኤን የተናገረው፡፡