ከ2 ወራት በላይ በአንድ የህንድ አየር ማረፊያ የተኛው ጋናዊ ተጫዋች
ኦ.አር.ፒ.ሲ ለተባለው እግር ኳስ ክለብ ለመጫወት ነበር በ6 ወራት ኮንትራት ወደ ህንድ ያቀናው
ተጫዋቹ ስለ ጉዳዩ በሰሙ የከተማው ባለስልጣናት ወደ ሆቴል እንዲገባ ተደርጓል
ከ2 ወራት በላይ በአንድ የህንድ አየር ማረፊያ የተኛው ጋናዊው ተጫዋች ወደ ሆቴል ተመለሰ
ህንድ ሙምባይ ከተማ በሚገኘው ቻትራፓቲ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከ60 ለበለጡ ቀናት ያደረው ጋናዊ እግርኳስ ተጫዋች ከአየር ማረፊያው ወደ ሆቴል እንዲገባ ተደረገ፡፡
ራንዲ ዩዋን ሙለር ይሰኛል የተባለው ተጫዋቹ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በረራዎች መቋረጣቸውን ተከትሎ ወደ ሃገሩ ለመመለስ ባለመቻሉ ያለፉትን 2 ወራት በአየር መንገዱ እያደረ ማሳለፉ ተነግሯል፡፡
በያዝነው ሳምንት 23ኛ ዓመት የልደት በዓሉን የሚያከብረው ራንዲ ባሳለፍነው ወርሃ ህዳር ነበር ወደ ሙምባይ ያቀናው፡፡
ያቀናበት ምክንያት ደግሞ በደቡባዊ ህንድ ኬሬላ ከተማ ለሚገኘውና በምህጻረ ቃሉ ኦ.አር.ፒ.ሲ ለተባለው እግር ኳስ ክለብ ለመጫወት የሚያስችለውን የ6 ወራት ኮንትራት በመፈረሙ ነው፡፡
የወረርሽኙ ስርጭት መባባስ ግን የህንድ ቆይታውን እንዳሰበው አላደረገለትም፡፡
ስርጭቱን ታሳቢ ያደረጉ የእንቅስቃሴ እገዳዎች ከመጣላቸው በፊት ወደ ቤተሰቦቹ ለመመለስ በማሰብም ለመጋቢት 30 ቀን 2020 የበረራ ቲኬት ይቆርጣል፡፡ በረራው እንዳያመልጠውም 10 ቀናትን ቀድሞ በባቡር ወደ ሙምባይ ይጓዛል፡፡ ሆኖም በእጁ የነበረው ገንዘብ የጠቀሱትን ቀናት እንዳሰበው በከተማይቱ የሚያቆየው አልነበረም፡፡ ይህም ለመኝታ እጦት ዳርጎታል፡፡
‘‘ማንም የማውቀው አልነበረም ፤ፖሊሶችን ተመለከትኩናም የገጠመኝን ነገርኳቸው፤ እነሱም ወደ አየር ማሪፊያው እንድሄድ ነገሩኝ’’ ሲልም ነው የነበረውን የሚያስቀምጠው፡፡
ሆኖም ከ3 ቀናት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ወረርሽኙን የተመለከተ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁንና ለቀጣዮቹ 21 ቀናት በሃገር አቀፍ ደረጃ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴዎች እንደማይደረጉ ያስታውቃሉ፡፡
በአዋጁ መሰረትም ከህንድም ሆነ ወደ ህንድ የሚደረጉ ዓለም አቀፍ በረራዎች ሁሉ ተሰረዙ፡፡
ራንዲም በረራዎቹ ዳግም እስከሚጀመሩ ድረስ በአየር መረፊያው ለመተኛት ወሰነ፡፡ ያለፉትን ከ60 በላይ ቀናትም በዚያው አሳለፈ፡፡ ሆኖም ዛሬም ድረስ እገዳዎች ከመራዘማቸው ውጪ በረራዎቹ ሊጀመሩ አልቻሉም፡፡
ስለ ጉዳዩ ያወቀውና በሙምባይ ያለው የጋና ቆንስል ጄነራልም በእንቅስቃሴ ገደቡ ምክንያት ወጣቱን እግርኳሰኛ ሊረዳው አልቻለም፡፡ ወጣቱ እግርኳሰኛም በገጠመው ነገር ተስፋ ሳይቆርጥ ወደ ሃገሩ ተመልሶ የሚበርባትን ቀን እየናፈቀ በዚያው መቆየቱን ቀጠለ፡፡
በአየር ማረፊያው አካባቢ ያሉ ሰዎች ድጋፍ ግን አልተለየውም ነበር፡፡ የሚመገበውን ይሰጡት የሚያስፈልገውን ያግዙትም ነበር፡፡
አንድ የአየር መንገዱ የደህንነት መኮንን የነገረውን ምክረ ሃሳብ ተቀብሎ ከሰሞኑ ‘ትዊተር’ በተሰኘው የማህበረሰብ ትስስር ገጽ ያሰፈራት መልዕክት ግን ታሪክ ቀየረች፡፡
መልዕክቷን የተመለከተ አንድ የአካባቢው ጋዜጠኛ የድረሱልኝ ጥሪውን ተጋርቶ ለአካባቢው የአስተዳደር አካላት በማጋራቱ የሙምባይ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ጉዳዩን እንዲያውቁት ሆኗል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ደግሞ ሙምባይ ከምትገኝበት የማሃራሽትራ ግዛት ሚኒስትሮች መካከል የአንደኛው ልጅ ናቸው፡፡
በዚህም ምክንያት ራንዲ በሰዓታት ውስጥ በረራ እስከሚጀመር ድረስ ያለ ምንም ችግር ሊቆይ ወደ የሚችልበት ሆቴል ገብቷል፡፡
የፈረመው ኮንትራትም ተጠናቋል፡፡ ከቤቴ የወጣሁት ቤተሰቦቼን ለማገዝ ነው የሚለው ራንዲ ግን አሁንም አዲስ ኮንትራትን ሊሰጠው የሚችል ካለ ወደ ህንድ እንደሚመለስ መናገሩን ሲ.ኤን.ኤን ከትቧል፡፡