የመንትዮቹ ወላጅ እናት የኮሮና ቫይረስ ታማሚ ነበሩ
ህንዳውያኑ መንትዮች ’ኳራንታይን‘ እና ’ሳኒታይዘር‘ የሚል ስም ወጣላቸው
በህንድ ኡታር ፕራዴሽ ይኖራሉ የተባለላቸው ጥንዶች ከሰሞኑ የተወለዱ መንትያ ልጆቻቸውን ’ኳራንታይን‘ እና ’ሳኒታይዘር‘ ሲሉ ስም አውጥተውላቸዋል፡፡
ስሙ መላው ዓለምን እያስጨነቀ ካለው የኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የተሰጠ ነው፡፡
ለምን እንዲህ ሊሏቸው እንደቻሉ ለቀረበላቸው ጥያቄም ጥንዶቹ “ሁለቱም ወረርሽኙን ለመከላከል እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ናቸው” ብለዋል፡፡
“ስሞቹ የሰው ልጅ ከቫይረሱ ሊጠበቅ ከሚችልባቸው ወሳኝ ነገሮችጋር የተያያዙ ናቸው፤ እኔም ከመውለዴ በፊት በቫይረሱ ተይዤ ነበር” ብለዋል የመንትዮቹ እናት ቬኑ፡፡
“ሁለቱም ከቫይረሱ የምንከለልባቸው ናቸው” ያሉት ወላጅ አባት ዳርሜንድራ ደግሞ “ይህ ዘላቂና የእድሜ ልክ እንዲሆን እንፈልጋለን፤ ለልጆቻችን ያገኘናቸው ምርጥ ስሞችም ናቸው” በሚል ተናግረዋል፡፡
ገልፍ ኒውስ ሜሩት በተሰኘች ከተማ የሚኖሩት ጥንዶቹ ’ማኒ‘ የተባለች እንስት ህጻን ልጅም አለቻቸው ብሏል፡፡