ጂም ራትክሊፍ የማንቸስተር ዩናይትድን 25 በመቶ ድርሻ ገዙ
ብሪታንያዊው ቢሊየነር በክለቡ 300 ሚሊየን ዶላር ኢንቨስት እንደሚያደርጉና የክለቡን የአስተዳደር ስራ ኩባንያቸው እንደሚረከብ ተናግረዋል
ኳታራዊው ሼክ ጃሲም ቢን ሃማድ አል ታኒ ክለቡን ለመግዛት የያዙትን እቅድ ውድቅ ማድረጋቸውም ተሰምቷል
ብሪታንያዊው ቢሊየነር ጂም ራትክሊፍ የማንቸስተር ዩናይትድን 25 በመቶ ድርሻ ወይም አክሲዮን ለመግዛት ስምምነት ተፈራረሙ።
ራትክሊፍ ከግሌዘር ቤተሰቦች ጋር በደረሱት ስምምነት መሰረት በክለቡ 300 ሚሊየን ዶላር ኢንቨስት ያደርጋሉ ተብሏል።
ይህም ውጤት የራቀውን ክለብ ወደቀደመ ክብሩን በመመለስ ትርፋማ እንደሚያደርጋቸው ታምኖበታል።
የሰር ጂም ራትክሊፍ ኩባንያ “ኢኒዮስ” የማንቸስተር ዩናይትድ ክለብን አስተዳደር ስራዎች ተረክቦ እንደሚሰራም ተገልጿል።
“ከልጅነቴ ጀምሮ እየደገፍኩት ከኖርኩት ማንቸስተር ዩናይትድ ቦርድ ጋር በአስተዳደር ስራዎች በጋራ ለመስራት በመስማማታችን ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል” ብለዋል ራትክሊፍ።
የክለቡን ውጤታማነት ለመመለስም ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይና እውቀትን እንደሚጠይቅ በመጥቀስ ድርጅታቸው በተለያዩ ሊጎች ያካበተውን ልምድ በኦልትራፎርድ እንደሚተገብር ነው ያብራሩት።
ቢሊየነሩ የስምምነት ውሉ እንደተጠናቀቀ 200 ሚሊየን ዶላር፤ እስከ 2024 መጨረሻ ደግሞ 100 ሚሊይን ዶላር ለክለቡ ይከፍላሉ።
የግሌዘር ቤተሰቦች በህዳር 2022 ዩናይትድን ለመሸጥ ፍንጭ ከሰጡ በኋላ ከራትክሊፍ ጋር ክለቡን ለመግዛት ሲፎካከሩ የቆዩት ኳታራዊው ሼክ ጃሲም ቢን ሃማድ አል ታኒ ከፉክክሩ መውጣታቸውን አስታውቀዋል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ከሰር አሌክስ ፈርጉሰን መልቀቅ በኋላ አምስት ቋሚና ሶስት ጊዜያዊ አሰልጣኞችን ቢቀያይርም በ11 አመት ውስጥ ያሳካው አንድ የኤፍኤካፕ፣ ሁለት ሊግ ካፕ እና አንድ ዩሮፓ ሊግ ዋንጫዎችን ብቻ ነው።
ቀያዮቹ ሰይጣኖች ባለፉት ስድስት አመታት ለተጫዋቾች ዝውውር 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ቢያወጡም በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ እንኳን ከመሪው አርሰናል በ12 ነጥብ ዝቅ ብለው 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ከውጤት መራቁ ባሻገር የክለቡ እዳ ከ600 ሚሊየን ዶላር በላይ መድረሱ የግሌዘር ቤተሰቦች ላይ ተቃውሞውን አበርትቶት መቆየቱ ይታወሳል።
ከዩናይትድ የ25 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ የገዙት ጂም ራትክሊፍም “ማንቸስተር ዩናይትድ በእንግሊዝም ሆነ በአውሮፓ መድረክ ወደ ቀደመ ክብሩ እንዲመለስ እንሰራለን” ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።