የቀያዮቹ ሰይጣኖች አሰልጣኝ ቡድናቸው በስታንፎርድ ብሪጅ የገጠመው ሽንፈት ቁጭትና ንዴት በመፍጠር ለድል ሊያነሳሳ እንደሚገባ ተናግረዋል
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዘንድሮ ሻምፒዮንን ከሚለዩ ጨዋታዎች የሚመደበው ተጠባቂ ፍልሚያ በኦልትራፎርድ ይደረጋል።
በ48 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ማንቸስተር ዩናይትድ በ70 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን የያዘውን ሊቨርፑል 11 ስአት ከ30 ላይ ይገጥማል።
ባለፈው ሀሙስ በቼልሲ ባለቀ ስአት 4 ለ 3 የተሸነፈው ዩናይትድ በብሬንትፎርድም በ99ኛው ደቂቃ ጎል ተቆጥሮበት ነጥብ መጋራቱ ይታወሳል።
አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግም ከዛሬው የኦልትራፎርድ ትንቅንቅ በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተጫዋቾቻቸው ሊቨርፑልን ሲገጥሙ “በብስጭት” እንደሚሆን ተናግረዋል።
ቀያዮቹ ሰይጣኖች ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያጡት አምስት ነጥብ ቀያዮቹን በኦልትራፎርድ እንዲያሸንፉ እልህና መነሳሳት ሊፈጥር እንደሚገባውም ነው ያሳሰቡት።
ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነው የኤሪክ ቴን ሀግ ቡድን በቀጣይ አመት የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።
በፕሪሚየር ሊጉ አምስተኛ ደረጃን ከያዘው ቶትንሃም ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ዘጠኝ የደረሰ ሲሆን፥ በ32 ጨዋታዎች 60 ነጥብ አስመዝግቦ 4ኛ ደረጃን በያዘው አስቶንቪላም በ12 ነጥብ ተቀድሟል።
“ከፍተኛ ጥራት ያለው ጨዋታ ማድረግ እንችላለን፤ በፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ ቡድኖችን የማሸነፉ አቅምም አለን” ያሉት ሆላንዳዊ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ግን የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን የማረጋገጡ ጉዳይ ያበቃለት እንዳልሆነ ተናግረዋል።
የዛሬው የኦልትራፎርድ ጨዋታም በስታንፎርድ ብሪጅ በኮል ሃልመር የመጨረሻ ደቂቃ ጎሎች የገጠማቸውን አሳዛኝ ሽንፈት የሚያስረሳ እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የተመዘገበው ውጤት እያስታወስን በንዴት ወደ ሜዳ እንገባለን “ንዴቱንም ወደ ሃይል በመቀየር ውጤት እናመጣለን” ነው ያሉት።
ቴን ሀግ በ2022 ማንቸስተር ዩናይትድን ከያዙ በኋላ በኦልትራፎርድ ሁለት ጊዜ የየርገን ክሎፑን ሊቨርፑል ማሸነፍ መቻላቸው ይታወሳል።
የዛሬው የፕሪሚየር ሊግ ወሳኝ ጨዋታ በቀያዮቹ ሰይጣኖች አሸናፊነት የሚጠናቀቅ ከሆነ ለአርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ መልካም ዜና ይሆናል።
ጨዋታው በፕሪሚየር ሊጉ በርካታ ዋንጫዎች የማንሳት ክብርን ይዞ ለመቆየትም ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ከ2013 ወዲህ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ አላነሳም፤ በአንጻሩ ሊቨርፑል ለመጨረሻ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ በ2020 ማንሳቱ ይታወሳል።
ቀያዮቹ የ2023/24 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ካነሱ 20 ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ካነሱት ቀያዮቹ ሰይጣኖች ጋር ይስተካከላሉ።