ኬን ከቤሊንግሃም - የእንግሊዛውያኑ ኮከቦች ፍጥጫ
በሻምፒዮንስ ሊጉ የመጀመሪያ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ባየር ሙኒክ በአሊያንዝ አሬና ሪያል ማድሪድን ያስተናግዳል
ባየር ሙኒክ ከሪያል ማድሪድ ጋር በተገናኘባቸው ያለፉት ሰባት የሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች አንድም ጊዜ አላሸነፈም
አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲን በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜው የደረሱት ባየር ሙኒክና ሪያል ማድሪድ ዛሬ ምሽት በአሊያንስ አሬና የመጀመሪያ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
እንግሊዝ በዘንድሮው የሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የሚወክላት የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ባይኖርም ሁለት እንግሊዛውያን ተጫዋቾች ለፍጻሜው ለመድረስ ይፋለማሉ። የባየር ሙኒኩ ሃሪ ኬን እና የሪያል ማድሪዱ ወጣት ተጫዋች ጁድ ቤሊንግሃም።
የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አምበሉ ሃሪ ኬን ክለቡ በ12 አመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የቡንደስሊጋ ዋንጫውን ቢያጣም አስደናቂ ጊዜ እያሳለፈ ነው።
ጁድ ቤሊንግሃምም በመጀመሪያ አመት የበርናባው ቆይታው ቁልፍ ተጫዋች መሆኑን አሳይቷል።
የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጋሬት ሳውዝጌትም በዩሮ 2024 ሶስቱን አናብስት ለድል ያበቃሉ ተብለው የሚጠበቁት አጥቂዎች ለመመልከት ወደ ሙኒክ ያቀናሉ።
ቤሊንግሃም ሮናልዶን ይበልጥ ይሆን?
የቀድሞው የበርኒንግሃም እና ቦርሺያ ዶርትሙንድ አማካይ ባለፈው አመት ወደ ሪያል ማድሪድ በ86 ሚሊየን ፓውንድ ከተዘዋወረ በኋላ የአለማችን ድንቅ ወጣት ተጫዋች መሆኑን አሳይቷል።
እንግሊዛዊው አማካይ በሁሉም ውድድሮች 21 ጎሎችን አስቆጥሯል፤ በ36 ጨዋታዎች ላይ 10 ጎል የሆኑ ኳሶችንም አቀብሏል።
በላሊጋው በባርሴሎና ላይ ባለቀ ስአት ያስቆጠራቸው ጎሎችም በከዋክብት በተሞላው ክለብ በአጭር ጊዜ ስሙን በጉልህ ቀለም እንዲያጽፍ አድርገውታል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ በመጀመሪያ አመት የበርናባው ቆይታው ከቤሊንግሃም የተሻላ (33 ጎሎችን) ቢያስቆጥርም በዋንጫ የታጀበ አልነበረም።
ቤሊንግሃም በበኩሉ የላሊጋ ዋንጫውን ለመሳም ተቃርቧል፤ ሻምፒዮንስ ሊግ ለማንሳትም ሶስት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ብቻ ይቀረዋል።
በስምንት አህጉራዊ ውድድሮች አራት ጎሎችን ያስቆጠረው ቤሊንግሃም የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ለ15ኛ ጊዜ ወደ ስፔን መዲና ይዞ ለመመለስ ግን ከሀገሩ ልጅ ሃሪ ኬን ጋር ተፋጧል።
የባየር ሙኒኩ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል ክለባቸው ቤሊንግሃም ለማስቆም “የተለየ መላ” ይፈልጋል ማለታቸውም የተጫዋቹን የትኩረት ማዕከልነት ያሳያል።
የኬን ጎል የማምረት ግስጋሴ ይቀጥላል?
ከቶትንሃም ለባቫሪያኑ ክለብ በ100 ሚሊየን ዪሮ የፈረመው ሃሪ ኬን፥ በሙኒክ ከተጠበቀው በላይ ውጤታማ ሆኗል።
የቶትንሃም የምንጊዜም ግብ አስቆጣሪው በዚህ አመት በሁሉም ውድድሮች 42 ጎሎችን ለባየር ሙኒክ አስቆጥሯል። ይህም በሰሜን ለንደኑ ክለብ በ2017/18 የውድድር አመት ካስቆጠረው (41 ጎል) የላቀ ነው።
35ቱ ጎሎች በቡንደስሊጋው ያስቆጠራቸው ሲሆኑ ሮበርት ሎዋንዶውስኪ የያዘውን ክብረወሰን ለመስተካከል ስድስት ጎሎች ብቻ ይቀሩታል።
ባየር ሙኒክ የቡንደስሊጋ ዋንጫውን በባየር ሊቨርኩሰን መነጠቁ ቢረጋገጥም በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ኬን የሚያስቆጥራቸው ጎሎች የሎዋንዶውስኪን ክብረወሰን ለመስበር ወሳኝ ናቸው።
በ10 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ሰባት ጎሎችን ያስቆጠረውና ሶስት ጎል የሆኑ ኳሶችን ያቀበለው ሃሪ ኬን፥ ግብ በ2023/24 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በርካታ ጎሎችን በማስቆጠር የሚቀድመው ኪሊያን ምባፔ (8 ጎሎች) ብቻ ነው።
ይሁን እንጂ የባቫሪያኑ ክለብ ከሪያል ማድሪድ ጋር በተገናኘባቸው ያለፉት ሰባት የሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች አንድም ጊዜ አላሸነፈም፤ በስድስቱ ተሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይቷል።