ቻይና ውሳኔውን ያሳለፈችው ብሪታኒያ የሆንግኮንግ ነዋሪዎችን የቪዛ ጥያቄ ምላሽ ልትሰጥ መወሰኗን ተከትሎ ነው
ብሪታኒያ ከዚህ ቀደም በቅኝ ግዛት ታስተዳድራት ለነበረችው የሆንግ ኮንግ ግዛት የምትሰጠው ፓስፖርት ከሁለት ቀናት በኋላ እውቅና እንደማይኖረው ቻይና አስታወቀች፡፡
የብሪታንያ ብሔራዊ የውጭ ሀገር ፓስፖርት ወይም በአጭሩ ‘ቢኤንኦ’ (BNO) በመባል የሚታወቀው እና ለሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች በብሪታኒያ የሚሰጠው ፓስፖርት ከጥር 23 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እንደጉዞ ዶክመንትም ይሁን እንደ መታወቂያ እንዲያገለግል ቻይና እንደማትፈቅድ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዣኦ ሊዢያን ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባዩ “ብሪታንያ የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎችን የብሪታንያ ሁለተኛ ዜጋ ለማድረግ ማቀዷ ለፓስፖርቱ የነበረንን መረዳት እንድንቀይር አድርጎናል” ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ የቻይናን ሉዓላዊነት መጋፋት እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ ብሪታንያ በፓስፖርቱ አማካኝነት በቻይና እና የራስ ገዝ አስተዳደር ባላት ሆንግ ኮንግ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባቷም ባለፈ ድርጊቱ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረር ስለመሆኑም ዣኦ ሊዢያን ተናግረዋል፡፡
ዘ ናሺናል እንደዘገበው በአዲሱ ቪዛ 300,000 ያክል የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ወደ ዩኬ እንደሄዱ ይገመታል፡፡
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ፣ “የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች በእንግሊዝ እንዲኖሩ ፣ እንዲሰሩ እና ቤታቸውን እንዲያንጹ አዲስ መንገድ በመፈጠሩ ከፍተኛ ኩራት ይሰማኛል” ብለው ነበር፡፡
“ይህን በማድረጋችን ከሆንግ ኮንግ ህዝብ ጋር ያለንን ታሪካዊ ግንኙነት እና ወዳጅነት ከማሳየታችን ባለፈ ለነጻነት እና ራስን በራስ ለማስተዳደር ፍላጎት መቆማችንን አመልክተናል” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ቻይና ውሳኔውን ያስተላለፈችው ፣ ብሪታንያ ለረዥም ጊዜ ከሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች የቀረበውን የቪዛ ጥያቄ ማስተናገድ ልትጀምር ሁለት ቀናት ሲቀሯት ነው፡፡ ይህም እስከ 5.4 ሚሊዮን የሚሆኑ የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች የብሪታኒያን ዜግነት እንዲያገኙ በር ይከፍታል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡
ቻይና ያሳለፈችው አዲስ ውሳኔ በቤጂንግ እና በለንደን መካከል ያለውን ፖለቲካዊ አለመግባባት የሚያሰፋ ነው ተብሏል፡፡