ሕንድ እና ቻይና ከአወዛጋቢው የድንበር አካባቢ ወታደሮቻቸውን እያስወጡ ነው
የኑክሌር መሳሪያ ባለቤት የሆኑት ሕንድ እና ቻይና በድንበር ጉዳይ ለረዥም ዓመታት ሲወዛገቡ ቆይተዋል
ሁለቱ ሀገራት በርካታ ወታደሮችን እና የጦር መሳሪያዎችን ድንበር ላይ አስፍረው ነበር
ሕንድ እና ቻይና በምዕራባዊ ሂማላያ ከሚወዛገቡበትአካባቢ ወታደሮቻቸውን ወደ ኋላ ለመመለስ መስማማታቸውን የሕንድ መከላከያ ሚኒስትር ዛሬ ሐሙስ የካቲት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ገለጹ፡፡
ሁለቱ ሀገራት በአወዛጋቢው ድንበር አካባቢ ለ አንድ ወር ወታደሮቻቸውን አስፍረው ቆይተዋል፡፡ በወታደራዊ አመራሮች እና በዲፕሎማቶች መካከል ብዙ ድርድሮች መደረጋቸውን ተከትሎ ነው ሁለቱ የኑክሌር መሳሪያ ባለቤት ተጎራባች ሀገራት ስምምነት ላይ የደረሱት፡፡
“ከቻይና ጋር ባደረግነው ውይይት በአወዛጋቢው እና 4,270 ሜትር ከፍታ ባለው የበረዶ ሐይቅ ሰሜናዊ እና ደቡባዊ ዳርቻዎች ጣልቃ-ገብነትን ለማስቀረት ስምምነት ላይ ተደርሷል” ሲሉ የሕንድ መከላከያ ሚኒስትር ራጅናት ሲንግ ተናግረዋል፡፡
የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር ደግሞ የሁለቱም ሀገራት ወታደሮች ከሐይቁ ዳርቻ ወደ ኋላ መመለስ መጀመራቸውን አስታውቋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በሐይቁ ሁለት ዳርቻዎች ላይ የገነቡትን የመከላከያ መዋቅሮች ለማፍረስም የተስማሙ ሲሆን ከእነዚህ መዋቅሮች ሁለት ሦስተኛው በቻይና ቁጥጥርስር የነበረ ነው፡፡
ሕንድ እና ቻይና በድንበሩ ጉዳይ ለረዥም ዓመታት ሲወዛገቡ ቆይተዋል፡፡ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ በተፈጠረ ግጭት 20 የህንድ ወታደሮች ተገድለዋል፡፡ በቻይናም በኩል በግልጽ ያልተጠቀሱ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1962 በዚሁ የድንበር ጉዳይ ከፍተኛ ውጊያ ያደረጉት ሀገራቱ በቅርቡ በርካታ ወታደሮቻቸውን ፣ እና ታንኮችን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ድንበር አስጠግተው ነበር፡፡
ዘ ናሺናል እንደዘገበው ሀገራቱ ከ1962ቱ ጦርነት ወዲህ ድርድሮችን ቢያደርጉም 3,500 ኪሎ ሜትር በሚረዝመው ድንበራቸው ጉዳይ እስካሁን ድረስ ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም፡፡