በመጀመሪያው ዙር ብቻ 10 ሺ ስራ አጦችን ለሚያሳትፈው ለዚህ ፕሮግራም 900 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል
የብሔራዊ በጎፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ምዝገባ ተጀመረ
ለአንድ ዓመት ያህል ጥናት ተደርጎበታል የተባለለት ብሔራዊ የበጎፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ምዝገባ መጀመሩን ፕሮግራሙን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫን የሰተው የሰላም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ፕሮግራሙ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ሲደረግበት የቆየ መሆኑን የገለጸው ሚኒስቴሩ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ ማወቅ ስለመቻሉም አስታውቋል፡፡
በሚኒስቴሩ የተጠሪ ተቋማት እና የስትራቴጂክ አጋርነት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ጄነራል የሆኑት ወ/ሮ አስማ ረዲ ፕሮግራሙ የተለያዩ የሙያ ባለቤት የሆኑ ወጣቶችን በማብቃት የሀገር እና የሕዝብ ፍቅርን፣ ምክንያታዊነትን፣ የሕይወት መምራት ክሕሎትን ፣ የሥራ ባሕልን፣ ሥነምግባር እና የሰላም እሴትን በማጎልበት ሃገራዊ አንድነትን፣ ብሔራዊ መግባባትን እና ጥልቅ ማሕበራዊ ትስስርን ለማጎልበት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፕሮግራሙ በመላው ሃገሪቱና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች እንደሚተገበር የገለፁት ወ/ሮ አስማ የምዝገባ ሂደቱ በየወረዳው ባሉ የሰላምና የፀጥታ ቢሮዎች በቀጥታ እና በኦንላይን ጭምር እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።
ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተመርቀው ስራ በመፈለግ ላይ ያሉ ወጣቶች ይሳተፉበታል ያሉም ሲሆን በመጀመሪያ ዙር እስከ 10ሺህ ስራ ፈላጊዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑም ተናግረዋል፡፡
ሀገር በዜጎች ምናብ ውስጥ ትገነባለች ያሉት የሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ መግባባት እና ማህበራዊ ሀብት ግንባታ ዳይሬክቶሬት ጄነራል አቶ ተግባሩ ያሬድ በበኩላቸው ፕሮግራሙ ምናባዊ ትስስርን ወደ ተግባራዊ ትስስር ለማምጣት የጎላ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል ፡፡
በፕሮግራሙ የመጀመሪያ ዙር የሚሳተፉ 10ሺህ ሰዎች ከተመዘገቡ በኋላ ለተከታታይ ሶስት ወራት ተግባቦትንና መልካም ዕሴትን የተመለከቱ ስልጠናዎችን የሚወስዱ ሲሆን በተመረጡ የስፖርት ባለሙያዎች የአካል ብቃት ስልጠናዎች እንደሚሰጧቸውም አቶ ተግባሩ ተናግረዋል፡፡
ከስልጠናው በኋላ ተሳታፊዎቹ ለአንድ ዓመት ያህል በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በመንቀሳቀስ በሙያቸው አገልግሎት የሚሰጡም ይሆናል፡፡
ተሳታፊዎቹ ሃገራቸውንና ህዝባቸውን የሚያውቁበት፣ ለቀጣይ ህይወታቸው መሰረት የሚጥሉበት ነው የተባለም ሲሆን ከተለያዩ የስራ ዕድል ፈጠራ ተቋማት ጋር በማገናኘት የስራ እድል እንደሚመቻችላቸውም ተጠቁሟል፡፡
በመጀመሪያው ዙር ብቻ እስከ 900 ሚሊዮን ብር እንደሚፈልግ በተነገረለት በዚህ ፕሮግራም ተሳታፊዎቹ ለመኖር የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ጨምሮ የኪስ ገንዘብ ያገኛሉ፡፡
የተሳታፊዎቹን ደህንነትና ሰላም ለማስጠበቅም ከማህበረሰቡ፣ ከክልልና ከፌዴራል መንግስታት ጋር በቅርበት በመሆን እየተሰራ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
ቀጣይነት አለው የተባለለት የፕሮግራሙ የመጀመሪያ ዙር ከ10 እስከ 15 ባሉት ቀጣይ ቀናት በሀገር አቀፍ ደረጃ ይፋ የሚደረግ ሲሆን ፕሮግራሙ ከፖለቲካ ተፅኖ ሙሉ በሙሉ ነፃ ነው ተብሏል፡፡