የኃይማኖት ተቋማት ከፉክክርና ከእልህ ይልቅ ስለ ይቅርታና ስለመቻቻል መስበክ ላይ እንዲያተኩሩ ተጠየቀ
በኢትዮጵያ የኃይማኖትና የሰው ልጆች ግንኙነት ሰላማዊና የቆየ ታሪካዊ ዳራ አለው፡፡
ሀገሪቱ ክርስትናንም እስልምናንም ተቀብላ በአብሮነት የማስተናገድ የቆየና የሚመሰገን ታሪክ እንዳላት ይታወቃል፡፡
ይሁንና ይህ የቆየ የሀገሪቱ እሴት አሁን ላይ ችግር እየገጠመው ስለመሆኑ ማሳያዎች እየተስተዋሉ ነው፡፡
ለአብነትም የቤተ እምነቶች መቃጠልና በአንዳንድ ቦታዎች ያሉ ታሪክንና አብሮነትን ያላገናዘቡ ጥላቻዎች ይስተዋላሉ፡፡
እነዚህ ሙሉ ለሙሉ በሀገሪቱ ያለውን አጠቃላይ ገጽታ ባያሳዩም ፈተና ግን እየሆኑ ናቸው፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና የዜጎችን አብሮ የመኖር እሴት ለማጠናከር የውይይት መርሃ ግብሮች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡
የሠላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጋር በመተባበር ኃይማኖቶች ለሠላም በሚል መሪ ቃል የውይይት መድረክ ዛሬ ጥር 04 ቀን 2012 በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
በዚህ መርሃ ግብር ላይ የኃይማኖት አባቶች፣ ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና የመንግስት ተወካዮች የተገኙ ሲሆኑ ሁሉም ተከባብሮና ተቻችሎ ቀድሞ የነበሩ እሴቶችን እንዲያስቀጥል ተጠይቋል፡፡
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አልማዝ መኮንን በሰላም አብሮ የመኖር ባህል አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸው በህዝብ መካከል መጠራጠርና አለመተማመን እንዲኖር የሚሰሩ ሃይሎችን መታገል ይገባል ብለዋል።
የኃይማኖት አባቶች ለሚሰሩት ስራ መንግስት አድናቆት አለው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ የኃይማኖት አባቶች ለሀገር ሰላምና ለህዝብ አብሮነት ከቀደመው በበለጠ መስራት አለባጣ ብልዋል።
ከዚህ ባለፈም ለዘመናት የቆየውን አብሮ የመኖርና የመቻቻል እሴቶችን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፈ ከሀይማኖት አባቶችና መሪዎች የሚጠበቅ ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበትም ነው የተባለው።
የኃይማኖት አባቶች ክፉና መጥፎ ተግባራትን ማስወገድና ከነዚህም መራቅ እንደሚያስፈልግ ገለጸው ሁሉም ስለ አብሮነትና ስለመከባበር ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ረጅሙን የመቻቻል ታሪክ መነሻ በማድርግም ለሀገር አንድነትና ህልውና በጋራ መቆም እንደሚገባም ነው የኃይማኖት አባቶች የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች ህብረት ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ከፉክክርና ከእልህ ይልቅ ስለ ይቅርታና ስለመቻቻል መስበክ ለሀገር አንድነት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲካሱና ይቅርታ እንዲሰፍን ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል ፕሮፌሰሩ፡፡
በመጨረሻም የኃይማኖት አባቶቹ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ የእምነት ተቋማት ላይ የደረሱ ጥቃቶች እና ሰሞኑን የታገቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን እገታ አውግዘዋል፡፡
በጥቅሉ በመድረኩ ላይ በሀገሪቱ ብሔራዊ መግባባት እንዲመጣ ከስሜት ይልቅ አርቆ አስተዋይነት ሊኖር እንደሚገባ ተገልጿል፡፡