በድሬዳዋ በድጋሚ ባጋጠመ የአጥር ግንብ መደርመስ አደጋ የ2 ወር ጨቅላ ህጻንን ጨምሮ የ3 ሰዎች ህይወት አለፈ
ከአሁን ቀደም በተደረመሰ የግንብ አጥር ምክንያት የ9 ሰዎች ህይወት ማለፉ የሚታወስ ነው
በመብረቅ አደጋ ምክንያት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉም ተገልጿል
በድሬዳዋ ከተማ በትናንትናው እለት በጣለው ከባድ ዝናብ ሳቢያ የአንድ መኖሪያ ቤት አጥር ግንብ ፈርሶ በመኖሪያ ቤት ላይ በመውደቁ የሰዎች ህይወት አለፈ፡፡
በአደጋው የ3 ሰዎች ህይወት ማለፉን የድሬደዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
አደጋውን በማስመልከት ዛሬ መግለጫን የሰጡት የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ አደጋው ቀበሌ 08 ልዩ ስሙ ለገሃሬ ከመንገድ በላይ ተብሎ በሚጠራው የከተማው አካባቢ ያጋጠመ ነው ብለዋል፡፡
ከሌሊቱ 9፡00 ጀምሮ ሲጥል በነበረው ከባድ ዝናብ ምክንያት የአንድ መኖሪያ ቤት አጥር ተደርምሶ በአቅራቢያው ባለው መኖሪያ ቤት ላይ በመውደቁ በቤቱ ውስጥ ተኝተው የነበሩ የአንድ ቤተሰብ አባላት ህይወት አልፏል፡፡
ህይወታቸው ካለፈው የቤተሰብ አባላት መካከል የ12 አመት፣ የ3 አመት እና የ2 ወር ጨቅላ ህጻን ይገኙበታል፡፡
የልጆቹ ወላጅ እናት እና አንድ ወንድ ልጃቸው ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ድሬዳዋ ድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል በህክምና ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
በልጆቹ አባት ላይ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱንም ነው ኮማንደር ገመቹ የተናገሩት፡፡
ኮማንደር ገመቹ አያይዘውም በመብረቅ አደጋ ምክንያት የአንድ ሰው ህይወት አልፏል ብለዋል፡፡
አደጋው ቀበሌ 01 መልካ ጀብዱ ከቀኑ 9፡00 አካባቢ በኢትዮ- ጅቡቲ ምድር ባቡር ግቢ ውስጥ ነው የደረሰው፡፡
በአደጋው በባቡር ጣቢያው ቅጥር ግቢ ውስጥ በስራ ላይ የነበሩ አንድ ግለሰብ ህይወት ሲያልፍ አንድ ሌላ ግለሰብ ደግሞ ለአካል ጉዳት ተዳርገው በማርያም ወርቅ ሆስፒታል በህክምና ላይ ይገኛሉ፡፡
በድሬዳዋ ከሰሞኑ ተመሳሳይ የአጥር ግንብ መደርመስ አደጋ አጋጥሞ የ9 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡
ኮማንደር ገመቹ የጎርፍ አደጋ ጭምር ሊያጋጥም እንደሚችል በማስታወስ ህብረተሰቡ ተገቢው ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡