ማሻሻያው ተደጋግመው የሚጠቀሱ ችግሮችን ለመፍታት ያስችል ይሆን?
በ1996 የወጣው ቻርተር ማሻሻያ ተጠናቋል ማሻሻያው ተደጋግመው የሚጠቀሱ ችግሮችን ለመፍታት ያስችል ይሆን?
ከሰሞኑ ፍጻሜውን ባገኘው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 44ኛ መደበኛ ጉባኤ ከተነሱ ዋነኛ የውይይት አጀንዳዎች መካከል አንዱ የድሬዳዋ ከተማ የአስተዳደር ቻርተር ጉዳይ ነው፡፡
ሐምሌ 23 ቀን 1996 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታውጆ የወጣው ቻርተሩ በወቅቱ የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች የሚያነሱትን የባለቤትነት ጥያቄ ታሳቢ አድርጎ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ለመጠበቅ፣ የከተማዋን የአስተዳደር አደረጃጀት ከዴሞክራሲና ከመልካም አስተዳደር መርሆዎች ጋር ለማጣጣም ይህንንም በሕግ ለመወሰን የሚሉ መነሻዎች አሉት፡፡
ከተማዋ እንዴት ልትተዳደርና መዋቅሯ ምን ሊመስል እንደሚችልም ይደነግጋል፡፡ ሆኖም ዓይነተ ብዙ ጥያቄዎች ተደጋግመው ይነሱበታል፡፡ ምክር ቤቱም ይህንኑ እንደ አንድ አጀንዳ አድርጎ መወያየቱን የአል ዐይን አማርኛ ምንጮች አመልክተዋል፡፡
ከቻርተሩ ጋር በተያያዘ ምን መከረ በሚል ስለ ጉዳዩ የጠየቅናቸው የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ ከተያዘው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ሲሰራ የነበረው የቻርተሩ ማሻሻያ ተጠናቋል ብለዋል፡፡
ማሻሻያው ለሁሉቱ ምክር ቤቶች (ለህዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን) ይላካል ያሉም ሲሆን ምክር ቤቱ ማሻሻያውን ለማጸደቅ የሚያስችሉ ቀጣይ የቤት ስራዎች በትኩረት መሰራት አለባቸው ስለማለቱም ገልጸዋል፡፡
ቻርተሩ ነዋሪውን በወጉ ከመወከል፣ በፍትሃዊነት እንዲገለገል ከማስቻል እና ከሌሎች ጉዳዮችም ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡ እንዲያውም ቻርተሩ ተዘንግቶ ነዋሪውን ባላማከለና ተጠቃሚነቱንም ባላረጋገጠ መልኩ የመፈጸሙ ተግባራት እንዳሉም ነው በራሱ በነዋሪው አንደበት ተደጋግሞ የሚነገረው፡፡
ይህን መሰሉ ችግር በተለይ “የድሬዳዋ ችግር ከቻርተሩ ጋር የተያያዘ ነው” የሚሉት የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሃመድ ቡህ ማሻሻያው ለወትሮው በፈጣን የንግድ እንቅስቃሴዋ የምትታወቀውን ከተማ በድጋሚ ለማነቃቃት እንደሚያስችል ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
ድሬዳዋን የምስራቁ የሃገሪቱ ክፍል የንግድ ማዕከል ለማድረግ የቻርተሩ ጉዳይ መፈታት በእጅጉ እንደሚጠቅምም ነው ምክትል ከንቲባው የተናገሩት፡፡
“የተወሰዱብንን የትራንስፖርት እና ሰነዶችን መሰል የፌዴራል ተቋማት ለማስመለስ ያስችለናል”ም ይላሉ፡፡ ከአስተዳደሩ የሚሰበሰቡ ገቢዎችን ከፌዴራሉ መንግስት በመጋራት ረገድ ያሉ ችግሮችን በመቅረፍም ቢሆን ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል፡፡
“ትላልቅ የንግድ ተቋማት አሉ የአካባቢውን ሃብት ይጠቀማሉ መስተዳድሩ ግን ምንም እያገኘ አይደለም፤ ገቢ አይጋራም፡፡ ለክልሎች እስከ 30 በመቶ ፈሰስ የሚደረግበትን ቀመር (ፌዴሬሽን ምክር ቤት ገቢ የሚያከፋፍልበትን ቀመር) እኛ አጥተናል፡፡ እሱን ካገኘን ያለብንን የበጀት እጥረት ለመቅረፍ እንችላለን፡፡ ከተማችንን በፍጥነት ለማሳደግ ብዙ ቤቶችን፣ መንገዶችን ለመስራት፣መሰረተ ልማት ለመዘርጋት እንችላለን” ሲሉም ነው የሚያስቀምጡት፡፡
አፈ ጉባዔዋ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋም በዚሁ ሃሳብ ይስማማሉ፡፡
“ድሬዳዋ ውስጥ ያለ አስፓልት ሙሉ የሚጠገነው በአስተዳደሩ ነው፡፡ ለምሳሌ እስከ 3 ሺ ባጃጅ ድረስ ለወጣቱ ስራ ዕድል ፈጠራ አስተዳደሩ ነው ከራሱ ወጪ የፈቀደው፡፡ ነገር ግን ያለው ገቢ ወደ ፌዴራል ነው የሚገባው፡፡ ከተማዋ በኢኮኖሚ ማደግ ያቃታት ለዚህ ነው የጋራ ገቢ ስለሌላት ነው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ነው ቻርተሩን ‘ሪቫይዝ’ ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያቱ” ሲሉ ያስቀምጣሉ፡፡
አፈ ጉባዔዋ የማሻሻያውን አስፈላጊነት አጠናክረው ሲያስረዱ ቻርተሩ ድሬዳዋ ከተማዋን እንጂ በአስተዳደሩ ስር ያሉ የገጠር ቀበሌዎችን አያውቅም ይላሉ በአስተዳደሩ ስር ያሉ 38 የገጠር ቀበሌዎችን ለማቀፍ የሚያስችል አስተዳደር ለማድረግ እንደሚያስችል በማከል፡፡
በድሬዳዋ ፍትሃዊ የውክልና ጥያቄዎች ተደጋግመው ይነሳሉ፡፡ በተለይም ፖለቲካዊ ውክልና የበርካቶች ጥያቄ ነው፡፡ “40-40-20” የተሰኘ የስልጣን መከፋፈያ ቀመር እንዳለም ነው የሚነገረው፡፡ ቀመሩ የአስተዳደሩ የስልጣን ድርሻ 40 በመቶ ለኦሮሞ፣ 40 በመቶው ለሶማሌ ቀሪው 20 በመቶ ደግሞ ለሌሎች በመስጠት የሚሰራበት ነው ይባላል አሰራሩን ደጋግመው ከሚወቅሱ ሰዎች አንደበት እንደሚደመጠው ከሆነ፡፡
ተጠናቋል የተባለው የቻርተሩ ማሻሻያ ይህን በፍትሃዊነት የመወከል ፖለቲካዊ ጥያቄ ምን ያህል ሊፈታው እንደሚል የጠየቅናቸው ወ/ሮ ፈጡምም ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
“እሱ ይፈታል ‘ኦልሬዲ’ አሁን ብልጽግና ፓርቲ ነው ያለው፡፡ በብልጽግና አስተሳሰብ ነው መዋቅር የሚሰራው ይህም ይመልሰዋል ብለን እናስባለን፡፡ 40-40-20 ጥያቄ ሊሆን የሚችልም አልነበረም፤ እሱ የፖለቲካ ጉዳይ ስለሆነ፡፡ እኛ ግን ሁሉም ውክልና ‘አን ኢቭን’ ከፓርቲ ውክልናም ጋር ፓርቲ ጽህፈት ቤት ውስጥም ሁሉም ብሄር ብሄረሰብ ውክልና ያለበት ሁኔታ አለ በአስተዳደሩ በአደረጃጀትም እየተሰራ ስለነበር ይፈታዋል”፡፡