ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፤ የተመድ ሰራተኞችን ገድለዋል ያለቻቸው 51 ዜጎቿ በሞት እንዲቀጡ ወሰነች
ቺሊ-ስዊዲናዊቷ ዛይዳ ካታላን እና አሜሪካዊው ሚካኤል ሻርፕ በወቅቱ የተገደሉ የተመድ ሰራተኞች ነበሩ
ተመድ ፍትህ ለማግኘት የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ በዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ በኩል በወቅቱ መግለጹ ይታወሳል
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተመድ ሰራተኞችን ገድለዋል ባለቻቸው ዜጎቿ በሞት እንዲቀጡ ፍርድ መስጠቷ ተሰምቷል።
ሀገሪቱ የሞት ቅጣት የበየነችው 51 በሚሆኑ ሰዎች ላይ ሲሆን፤ ሁሉም “እንደፈረንጆቹ 2017 በካሳየ ግዛት የተነሳውን ብጥብጥ ተከትሎ በተመድ ሰራተኞች ላይ የግዲያ ወንጀል የፈጸሙ” ሚሊሻዎች ናቸው በሚል ነው።
የሞት ፍርድ የተወሰነባቸው ሰዎች ሽብር፣ ግዲያ እና የሰው አካላትን መቁረጥ የሚል ክስ እንደቀረበላቸውም ነው የፈረንሳዩ የዜና ወኪል/ ኤ.ኤፍ.ፒ/ ዘገባ የሚያመለክተው።
በፈረንጆቹ 2016 የካሳይ ግዛት ባህላዊ መሪ የነበሩትን ካምዊና ሳፑ ግዲያን ተከትሎ በተፈጠረውና በ2017 በቆመው ቀውስ ምክንያት፤ሁለት የተመድ ሰራተኞችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መገደላቸው እንዲሁም አንድ ሚሊየን ገደማ ሰዎች መፈረናቀላቸው ይታወሳል።
ከተገደሉት መከካል በርካታ የተመድ ሰራተኞች እንደሚገኝባቸውም የተመድ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የስዊዲንና-ቺሊ ዜግነት ያላት ዛይዳ ካታላን እና አሜሪካዊው ሚካኤል ሻርፕ በወቅቱ ታግተው በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ የተመድ ሰራተኞች ነበሩ
ሁለቱም የተመድ ሰራተኞች የተገደሉት፤ በሀገሪቱ መንግስት እና ታጣቂዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የጅምላ መቃብሮች በተባሉ ስፍራዎች ላይ ምርመራ በማካሄድ ላይ ሳሉ እንደነበርም ነው መረጃወች የሚጠቁሙት።
የተመድ ሰራተኞቹ ተርጓሚ በመሆን ስትሰራ የነበረችው ቤቱ ሺንተላም እንዲሁ አብራአቸው ተገድላለች። አስክሬናቸው የተገኘውም ከ16 ቀናት በኋላ ነበር።
በወቅቱ በሰራተኞቹ ላይ በተፈጸመውና ዘግናኝ በሆነው ድርጊት እጅግ የደነገጠው ተመድ፤ ፍትህ ለማግኘት የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ በዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ በኩል መግለጹ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት ላለፉት አራት ዓመታት በወታደራዊ ፍርድ ቤት ሲካሄድ የነበረው የፍርድ ሂደት መቋጫ አግኝቶ፤ አጥፊዎች የፍርድ ቤት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።