ጦርነቱ የተካሄደው ከ20 ዓመታት በፊት ቢሆንም የክስ ሂደቱ ውሳኔ ያገኘው ግን ዛሬ ነው
ኡጋንዳ ከፈረንጆቹ 1998 እስከ 2003 ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ባደረገችው ጦርነት ለጠፋው የሰው ሕይወት እና ለወደመው ሀብት ካሳ እንድትከፍል ተፈረደባት፡፡
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፤ ኡጋንዳ ካሳ እንድትከፍላት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፍትሕ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርባ የነበረ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ለኪንሻሳ ፈርዶላታል ተብሏል፡፡ ኡጋንዳ ለዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መክፈል አለባት የተባለው 325 ሚሊዮን ዶላር መሆኑም ነው ተገለጸው፡፡
ኪንሻሳ ምንም እንኳን ክሱን ብትረታም ይከፈለኝ ብላ አቅርባ ከነበረው 11 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ እንዲከፈላት የተወሰነው 325 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡
ኡጋንዳ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ባደረገችው ጦርነት፤ ለጠፋው የሰው ህይወት 225 ሚሊዮን ዶላር፤ ለንብረት ውድመት 60 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በጦርነቱ ለወደመው የተፈጥሮ ሀብት 60 ሚሊን ዶላር እንድትከፍል ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል ተብሏል፡፡
ጦርነቱ የተካሄደው ከ 20 ዓመታት በፊት ቢሆንም የክስ ሂደቱ ውሳኔ ያገኘው ግን ዛሬ ነው፡፡ ኡጋንዳ እና ሩዋንዳ የኮንጎ መንግስትን የሚቃወሙ አማጺያንን ሲደግፉ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሀገራቱ ይህንን ያደረጉት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቃዊ ክፍል በማዕድን የበለጸገችውን ኢቱሪን ለመቆጣጠር እንደነበር ይታወሳል፡፡
የተመድ ፍርድ ቤትም ኡጋንዳ፤ የዴሞክራቲክ ኮንጎ አካል የሆነችውን ኢቱሪን ዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስ መልኩ ለመቆጣጠር መሞከሯ ትክክል አለመሆኑን ገልጾ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር፡፡