የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋች አሁን ቄስ ሆኖ እያገለገለ ነው
ለማንቸስተር ዩናይትድ፣ ኖርዊች ሲቲ፣ ካርዲፍ ሲቲ የተጫወተው ፊል ሙልራይን እግር ኳስን እርግፍ አድርጎ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ሆኗል
የፍቅር አጋሩን ካጣ በኋላ የእግር ኳስ ህይወቱ ደስታን እንዳልስጠው ሙልራይን ይናገራል
ፊል ሙልራይን በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የራሱን ደማቅ አሻራ አኑሯል።
ለማንቸስተር ዩናይትድ ፈርሞ አንድ ጨዋታን ብቻ ቢጫወትም ለኖርዊች ሲቲ ከፈረመበት 1999 ጀመሮ ከ150 በላይ ጨዋታዎችን አድርጓል።
አማካዩ ሙልራይን ካርዲፍ ዳግም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንዲቀላቀል በማድረግም ስሙ ይነሳል። ለካርዲፍ ሲቲም በተጫወተባቸው ጊዜያት የጎላ ታሪክ ባይሰራም በእግር ኳስ ህይወቱ ደካማ የሚባል አልነበረም።
- ራሽፎርድ በማንቸስተር ዩናይትድ እስከ 2024 የሚያቆየውን አዲስ ኮንትራት ተፈራረመ
- አሰልጣኝ ቴን ሃግ “ዴቪድ ዴ ሂያ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር እንደሚቆይ ተስፋ አደረግላሁ” አሉ
በሰሜን አየርላንድ ብሄራዊ ቡድንም እንደ ፊል ሙልራይን የተሳካለት የለም ነው የሚባለው።
በፈረንጆቹ 2008 ከኖርዊች ሲቲ ሲለቅ ግን ከራሱ ጋር የመምከር እድል እንዳገኘ ይናገራል።
ከ600 ሺህ ፓውንድ በላይ ደመወዝ ያገኝ የነበረው ተጫዋች፥ የፍቅር አጋሩን ካጣ በኋላ የእግር ኳስ ህይወቱ ደስታን እንዳልስጠው ነው የሚገልጸው።
እናም በሰሜን አየርላንዷ መዲና ቤልፋስት ወደሚገኘው ኪዩን ዩኒቨርሲቲ በመግባት ፍልስፍናን ለሁለት አመት አጠና።
ሙልራይን ዩኒቨርሲቲ ከመግባቱ በፊት የኖርዊች ተጫዋች እያለ ሃብትና ዝናው ደስታን ሊሰጡት እንዳልቻሉ ነው ለኖርዊች ክለብ ድረገጽ የተናገረው።
“ሁሉ ነገር እያለኝ በወጣትነት እድሜዬ እንዴት ደስታ ራቀኝ ስል እጠይቅ ነበር” የሚለው ተጫዋቹ፥ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ እግር ኳስ አልተመለሰም።
ከእግር ኳስ ያላገኘውን ደስታ ወደ እምነቱ በመጠጋት ለማሳካት ወደ ካቶሊክ ቤተክርስቲያናት ደጋግሞ መመላለስን ተያያዘው።
በዚህም መንፈሳዊ እረፍትና ደስታን እያገኘ መምጣቱን የሚናገረው ተጫዋቹ በ2017ም በኮርክ ከተማ የምትገኘው የካቶሊክ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ቄስ ሆኖ ለማገልገል ቅስና ተቀብሏል።
እግር ኳስን እርግፍ አድርጎ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ለመሆን አመታት ወስደውብኛል የሚለው የቀድሞው ኮከብ ፊል ሙልራይን፥ የእግር ኳስ ከፍ እና ዝቅ በመንፈሳዊው አለም የለም ባይ ነው። በወጣትነቱ ጫማ ያስቀለው መንፈሳዊ አገልግሎትም እረፍትና ደስታን እንደሰጠው ተናግሯል።