የቤነፊካ እና ስፖርቲንግ ሊዝበን የሴቶች ቡድኖች ጨዋታ ላይ ነው ለመጀመሪያው ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው
አውሮፓዊቷ ሀገር ፖርቹጋል በእግር ኳስ ግጥሚያ ላይ ነጭ ካርድን ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ አውላለች።
የቤነፊካ እና ስፖርቲንግ ሊዝበን ሴቶች ቡድኖች ባደረጉት የደርቢ ጨዋታ ላይ ነው ካርዱ በጨዋታው ዳኛ የተመዘዘው።
ቤነፊካ በመጀመሪያው አጋማሽ 3 ለ 0 እየመራ በነበረበት ወቅት አንድ ደጋፊ ተዝለፍልፎ በመውደቁ የሁለቱም ቡድኖች የህክምና ባለሙያዎች በፍጥነት ድጋፍ ለመስጠት ይሯሯጣሉ።
ሁኔታው ጨዋታውን ለደቂቃዎች እንዲዘገይም ያደርጋል።
ጨዋታውን ሲመሩ የነበሩት ካታሪና ካምፖስም የህክምና ባለሙያዎቹ እንደተመለሱ ነጭ ካርድ መዘውባቸዋል።
ሁኔታው ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ እንደመሆኑ በስታዲዮ ደ ሊዩዝ የታደሙ በርካታ ደጋፊዎችን አስገርሞ እንደነበር ስካይ ኒውስ አስነብቧል።
ነጭ ካርድ ስፖርታዊ ጨዋነት እና ፍትሃዊነትን የሚያበረታታ መሆኑን የተረዱ ደጋፊዎች ግን ለዳኛው ውሳኔ ክብር ሰጥተው ምስጋናቸውን በጭብጨባ መግለጻቸውን ነው ዘገባው የጠቆመው።
የፖርቹጋል እግር ኳስ ፌደሬሽን በስፖርታዊ መድረኮች በጎምግባርን የሚያሳዩ ተጫዋቾችን እና የቡድን አባላትን ለማበረታታ ነው ነጭ ካርድ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደረገው።
ይህን ካርድ በስፖርታዊ መድረኮች እንዲመዘዝ በመወሰንም ፖርቹጋል ብቸኛ ሀገር ናት ተብሏል።
ከጨዋታ ውጭ የሚያደርገውን (ቀይ) እና ማስጠንቀቂያውን (ቢጫ) ካርድ ከመስጠት ባሻገር ስፖርታዊ ጨዋነትን ያጎለብታል የተባለውን ነጭ ካርድ ያስተዋወቀችው ሊዝበን፥ ባለፈው ቅዳሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጭ ካርድን መዛለች።