በሀገሪቱ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፈው ሳምንት ከነበረው የ 79 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል
ቤልጂየም አዲስ የኮሮናቫይረስ 'ሱናሚ' እየገጠማት ነው ተባለ
በመላ ሀገሪቱ የተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ እየሄደ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ቤልጅየም በኮሮናቫይረስ ልትሸነፍ ትችላለች ሲሉ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል ፡፡
ሚኒስትሩ ፍራንክ ቫንደንብሮክ እንዳሉት እንደ አዲስ እያገረሸ የሚገኘው የኮሮና “ሱናሚ” ከባለሥልጣናት ቁጥጥር ውጭ ለመሆን ተቃርቧል፡፡
ቤልጂየም እ.ኤ.አ. በዚህ ዓመት መጀመርያ በአውሮፓ የመጀመሪያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በጣም ከተጎዱ ሀገራት አንዷ ነች፡፡
ስርጭቱን ለመቆጣጠር አዳዲስ እርምጃዎች ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የተደረጉ ሲሆን ሁሉም መጠጥ ቤቶች እና ምግብ ቤቶች ለአራት ሳምንታት ዝግ ሆነው ይቆያሉ፡፡
ወረርሽኙን ለመቋቋም ከተዘጋጁ የመንግስት ገደቦች መካከል ከዛሬ ሰኞ ጥቅምት 09 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ማንኛውም ግለሰብ ከቤተሰብ አባላት ውጭ ከሌላ አንድ ሰው ጋር ብቻ እንዲገናኝ የሚል ይገኝበታል፡፡ ከተቻለ የሀገሪቱ ነዋሪዎች ስራቸውን ከቤት ሆነው እንዲሰሩም ተወስኗል፡፡
የቤልጂየም የጤና ተቋም ‘ሳይንሳኖ’ እንደሚለው ቤልጂየም ባለፉት ሰባት ቀናት በአማካይ 7,876 አዳዲስ ዕለታዊ ተጠቂዎችን ያስመዘገበች ሲሆን ይህም ባለፈው ሳምንት ከነበረው የ 79 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
በቫይረሱ ተይዘው ለህክምና ሆስፒታል የሚተኙ ሰዎች ቁጥርም በዛሬው ዕለት 2845 ሆኗል፡፡ የተጠቂዎች ቁጥር መጨመሩን ከቀጠለ ቤልጂየም እስከ ህዳር አጋማሽ ድረስ 2 ሺህ የጽኑ ህሙማንን የማስተናገድ አቅሟ እንደሚሞላ ባለስልጣናት ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሌክሳንደር ዴ ክሩ ለአንድ ሚዲያ እንደተናገሩት ሁኔታው ከዚህ ቀደም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እገዳ ከተጣለበት መጋቢት 18 ቀን በላይ የከፋ ነው፡፡
የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በመላው አውሮፓ እየጨመረ እና ቫይረሱ በፍጥነት እየተሰራጨ በመሆኑ በአህጉሪቱ አዳዲስ እገዳዎች እየተጣሉ ነው፡፡
ቫይረሱ ዳግም አገርሽቶባቸው እርምጃ እየወሰዱ ከሚገኙ የአውሮፓ ሀገራት መካከል ጣሊያን ትጠቀሳለች፡፡ በጣሊያን ከፍተኛው ዕለታዊ የተጠቂዎች ቁጥር መመዝገቡን ተከትሎ ትናንት እሑድ አዳዲስ ዕርምጃዎችን የወሰደች ሲሆን ዘጠኝ ዋና ዋና የፈረንሣይ ከተሞችም የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሎባቸዋል፡፡
በአህጉሪቱ ከፍተኛ የተጠቂዎች መጠን ያለባት ቼክ ሪፓብሊክ ሀገር-አቀፍ የእንቅስቃሴ ገደብ ለመጣል በመሰናዳት ላይ ነች፡፡
ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ሌሎችም ሀገራት በተለያየ መጠን ሁለተኛ ዙር እገዳዎችን በመጣል ላይ ናቸው እንደ ቢቢሲ ዘገባ፡፡