ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የአውሮፓ ሀገራት ዳግም እገዳዎችን መጣል ጀመሩ
ህብረተሰቡ መመሪያዎችን እንዲያከብር ያሳሰቡት ፖፕ ፍራንሲስም ለምዕመናን እንደወትሮው በቅርበት ሰላምታ አልሰጥም ብለዋል
በአውሮፓ ቫይረሱ ለሁለተኛ ጊዜ እያንሰራራ መሆኑ ተገልጿል
ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የአውሮፓ ሀገራት ዳግም እገዳዎችን መጣል ጀመሩ
ቫይረሱን በመከላከል ስኬታማ የነበሩ ሀገራትን ጨምሮ በአውሮፓ ዙሪያ የኮሮና ቫይረስ ለሁለተኛ ዙር በማንሰራራት ላይ ነው፡፡ ለአብነትም ፈረንሳይ በቅርቡ በአንድ ቀን ከ26 ሺህ በላይ ተጠቂዎችን ሪፖርት ስታደርግ ጀርመን እና ጣሊያን ደግሞ ከከ5 እና ከ6 ወራት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ቀን ከ5 ሺህ በላይ ተጠቂዎችን ሪፖርት አድርገዋል፡፡ ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ በዛሬው ዕለት 19 ሺህ 724 ተጠቂዎችን ሪፖርት አድርጋለች፡፡
ይህን ተከትሎ የተለያዩ ሀገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ያስችለናል ያሏቸውን እገዳዎች በድጋሚ መጣል ጀምረዋል፡፡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስም ህብረተሰቡ ማህበራዊ ርቀቱን እንዲጠብቅ እና የባለሙያዎችን ምክር እንዲተገብር ጠይቀዋል፡፡ “በርቀት ሰላም ብላችሁ ይቅርታ አድርጉልኝ ፤ ወትሮውን እንደማደርገው በአቅራቢያችሁ መጥ ሰላምታ ብሰጣችሁ ደስ ይለኝ ነበር ፤ ነገር ግን ርቀትን መጠበቅ መልካም ነው” ሲሉ ጳጳሱ ተናግረዋል፡፡
በስፔን ካታሎኒያ ግዛት ሁሉም መጠጥ ቤቶች እና ሬስቶራንቶች ለ15 ቀናት እንዲዘጉ ተወስኗል፡፡ በስፔን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር 900 ሺህ ገደማ መድረሱን ተከትሎ ነው ውሳኔው የተላለፈው፡፡ ባለፈው ሳምንትም ዋና ከተማዋ ማድሪድ እና በዙሪያዋ የሚገኙ አካባቢዎች በከፊል እንዲዘጉ ተደርጓል፡፡
ኔዘርላንድስ በካፌዎች፣ መጠጥ ቤቶች እና ሬስቶራንቶች ላይ የሰዓት ዕላፊ ገደብ አውጃለች፡፡ ከዚህም ባለፈ ማህበራዊ ጥግግትን የሚቀንሱ ሌሎች እገዳዎችን በመጣል ላይ ነች፡፡
ዩናይትድ ኪንግደም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚተገበር ሶስት አይነት ህግ ልትተገብር መሪዎዎቿ በመምከር ላይ ናቨው፡፡ በቫይረሱ ተይዘው ያገገሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ሶስት አይነት ህግ ያስፈለገው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቫይረሱ የስርጭት መጠን ስለሚለያይ መሆኑን በተወካዮች ምክር ቤት ለተነሳላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ አንስተዋል፡፡
የዩኬ አባላት የሆነችው ሰሜን አየርላንድ ከምሽት 4 ሰዓት በኋላ አልኮል መጠጦችን መሸጥ ከልክላለች፡፡ የሰርግ እና የቀብር ስነስርዓቶች ላይ ከ25 በላይ ሰዎች እንዳይገኙ፣ በሌሎች ዝግጅቶች ደግሞ መሰብሰብ የሚችለው ሰው ከፍተኛ ቁጥር 15 እንዲሆንም የወሰነች ሲሆን ሌሎች እገዳዎችንም ጥላለች፡፡
ስኮትላንድ ደግሞ ሰዎች ሰሜን ምዕራብ እንግሊዝ ወደምትገኘው የባህር ዳርቻ ከተማ ብላክፑል እንዳይሄዱ አስጠንቅቃለች፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ባለፈው ወር በስኮትላንድ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው 180 ሰዎች ብላክፑል ሔደው የተመለሱ በመሆናቸው ነው፡፡
ዌልስ ኮሮና ቫይረስ በስፋት ከተሰራጨባቸው የዩኬ የተለያዩ አካባቢዎች ከነገ ወዲያ ጥቅምት 06 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሰዎች እንዳይገቡ ተከልክሏል፡፡ እገዳው የእንግሊዝ ፣ የስኮትላንድ እና የሰሜን አየርላንድ አካባቢዎችን ያካትታል፡፡
ሌሎች ሀገራትም የተለያዩ እገዳዎችን መጣል ጀምረዋልእንደ ቢቢሲ ዘገባ፡፡