ወጣቶች የኮሮና ክትባትን እስከ 2022 ሊጠብቁ ይችላሉ - የዓለም ጤና ድርጅት
ከ2021 አጋማሽ በኋላ እንደሚገኝ የሚጠበቀው ክትባቱ በተጋላጭነት ልክ በቅደም ተከተል ይሰጣል ተብሏል
በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም መዘናጋት እንዳይኖር ድርጅቱ አሳስቧል
ወጣቶች የኮሮና ክትባትን እስከ 2022 ሊጠብቁ ይችላሉ - የዓለም ጤና ድርጅት
የዓለም ጤና ድርጅት ረቡዕ ዕለት በሰጠው መግለጫ ጤናማ ወጣቶች በአጠቃላይ ዝቅተኛ ተጋላጭነት ያለው የስነሕዝብ ክፍል ውስጥ ስለሚካተቱ የኮቪድ -19 ክትባትን ለማግኘት እ.ኤ.አ. እስከ 2022 ድረስ መጠበቅ ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል አስታውቋል፡፡
"ክትባቱ በቅድሚያ የሚሰጠው ለጤና ሰራተኞች እና የፊት መስመር የህክምና ሰራተኞች ነው፡፡ ከሜና ባለሙያዎችም ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸው ቀዳሚዎች ሲሆኑ ከዚያ በኋላ አዛውንቶች እና የመሳሰሉት እንደሚከተሉ አብዛኛው ሰው ይስማማበታል" ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ሳይንቲስት ሶሚያ ስዋሚናታን ተናግረዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ሳይንቲስት ሶሚያ ስዋሚናታን-ፎቶ ኤፒ
በመሆኑም ጤናማ ወጣቶች ክትባቱን እስከ 2022 ድረስ መጠበቅ ሊኖርባቸው ይችላል ነው ያሉት ሳይንቲስቷ፡፡ ክትባቱ ከ2021 አጋማሽ በኋላ በብዛት እንደሚገኝ እና ለህብረተሰቡ እንደሚዳረስ የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡
የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር እጅን መታጠብ ፣ ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ ፣ ጭምብሎችን ማድረግ እና ሌሎችንም ጥንቃቄዎች ከማድረግ ህብረተሰቡ እንዳይቦዝንም ድርጅቱ አሳስቧል፡፡
ስርጭቱን ለመግታት “ቢያንስ 70 በመቶውን ህዝብ መከተብ ያስፈልጋል” ያሉት ሳይንቲስቷ ስዋሚናታን በመሆኑም ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አስጠንቅቀዋል፡፡
ምንም እንኳን በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በሚያዝያ ወር በቀን ከ7,500 በላይ ከነበረበት በቀን ወደ 5,000 ያህል ቢወርድም ዶ / ር ስዋሚናታን ይህ ሊያዘናጋን አይገባም ይላሉ፡፡ በጽኑ ህሙማን የህክምና ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ታካሚዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑንም ጠቁመዋል ሲል ዘ ናሺናል ዘግቧል፡፡
እስካሁን በመላው ዓለም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ38.7 ሚሊዮን ሲበልጥ ከነዚህም ከ1.09 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ ከ29 ሚሊዮን የሚበልጡት አገግመዋል፡፡