ቤልጂየም ሴተኛ አዳሪዎች ጡረታ እና የወሊድ ፈቃድ እንዲያገኙ ፈቀደች
ሀገሪቱ ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ የወሲብ ንግድን ህጋዊ ማድረጓ አይዘነጋም
በዓለማችን ላይ 10 ሚሊዮን ሴተኛ አዳሪዎች እንዳሉ ተገልጿል
ቤልጂየም ሴተኛ አዳሪዎች ጡረታ እና የወሊድ ፈቃድ እንዲያገኙ ፈቀደች
የአውሮፓ ህብረት ዋና ከተማ መገኛ የሆነችው ቤልጂየም ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ የወሲብ ንግድን እንደ ማንኛውም የስራ ዘርፎች በህጋዊ መንገድ መስራት እንዲቻል መፍቀዷ ይታወሳል፡፡
ሀገሪቱ ዜጎች ወደ ወሲብ ንግድ ለመግባት ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ መያዝን እንደ መስፈርት ያስቀመጠች ሲሆን ህጉ በመጽደቁ አስቀድመው በድብቅ ሲሰሩ የነበሩ ተቋማት እና ግለሰቦች ደስተኞች መሆናቸውን በወቅቱ ተናግረው ነበር፡፡
በዚህ ህግ መሰረትም በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሰዎች አገልግሎቱን ለደንበኞቻቸው ለመስጠት ከተቋቋሙ ድርጅቶች እና ፈላጊዎች ጋር መዋዋል እንዲችሉ ተፈቅዶላቸዋልም ተብሏል፡፡
አሁን ደግሞ ሀገሪቱ በዚህ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች እንደ ማንኛውም ሰራተኞች የጡረታ ክፍያ፣ የጤና ደህንነነት ክፍያ፣ ዓመታዊ እረፍት፣ የህመም እና የወሊድ ፈቃድ ማግኘት እንዲችሉ ፈቅዳለች፡፡
ቢቢሲ በዚህ ሙያ የተሰማራች አንድ ሴትን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ በአዲሱ ህግ ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች፡፡
ባለትዳር እና ነፍሰጡር መሆኗን የተናገረችው ይህች ሴት በቅርቡ አምስተኛ ልጇን ለመውለድ በዝግጅት ላይ መሆኗን ገልጻ አዲሱ ህግ ከልጇን ጋር ረጅም ጊዜ እንድታሳልፍ እና በቂ እረፍት አድርጋ ወደ ስራዋ እንድመለስ ያደርገኛል ብላለች፡፡
ስራችን የማህበራዊ አገልግሎት መስጠን ነው የምትለው ይህች ሴት ከደንበኞቻችን ጋር አብሮ ጊዜ ማሳለፍ፣ ደንበኞቻችን ከሚወዷቸው ሙዚቃዎች ጋር መደነስ፣ የሚያወሩትን ማዳመጥ እና ሌሎችንም ፍላጎቶቻቸውን እያሟሉ መሆኗን ተናግራለች፡፡
ሴተኛ አዳሪዎች ጡረታ እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ በማደረግ ቤልጂየም በዓለም ላይ የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች፡፡
በዓለም ላይ 10 ሚሊዮን ሴተኛ አዳሪዎች አሉ የተባለ ሲሆን ጥቂት የዓለማችን ሀገራት የወሲብ ንግድን ህጋዊ አድርገዋል፡፡
በሂውማን ራይትስ ዋች አጥኚ የሆኑት ኢሪን ኪልብራይድ በበኩላቸው የቤልጂየም አዲሱ ህግ ጥሩ እርምጃ መሆኑን ገልጸው ሌሎች ሀገራትም የብራስልስን ጥረት እንዲከተሉ አሳስበዋል፡፡