ፎረፎር እና ሽበት መካቹ ቅርንፉድ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች
ቅርንፉድ በሶዲየም፣ ካልሺየም፣ ብረት እና ፎስፎረስ መበልጸጉ ለጸጉር እድገትና ጤና ወሳኝ ድርሻ እንዲኖረው አድርጎታል
የምግብ መፈጨት ችግር ላለባቸውና በራስ ምታት ለሚሰቃዩ ወገኖችም ቅርንፉድ በምግባቸው ውስጥ ባይጠፋ ይመከራሉ
ቅርንፉድ በእለት ተዕለት አመጋገባችን ውስጥ ባይጠፉ ከሚመከሩ ቅመሞች አንዱ ነው።
ለቆዳ ጤና ወሳኝ ድርሻ ያለው፣ የምግብ መፈጨትን የሚያፋጥነው፣ የአፍ ጠረንን መልካም የሚያደርገው ቅርንፉድ፥ ተዘርዝሮ የማያልቅ ጥቅሞች አሉት።
በኢትዮጵያውያን የአመጋገብ ስርአት ትልቅ ስፍራ ያለው ቅርንፉድ ለጸጉር እድገትም ትልቅ አበርክቶ አለው።
ብዙዎችን ለሚያስቸግረው ፎረፎርም ሆነ የጸጉር ሽበት የቅርንፉድ ቅባትን መጠቀም ይመከራል።
ቅርንፉድ በውስጡ የያዛቸው ሶዲየም፣ ካልሺየም፣ ብረት እና ፎስፎረስ ለጸጉር እድገትና ጤና ወሳኝ ናቸው።
ቅርንፉድ ለጸጉር የሚሰጣቸው ጥቅሞች
- በጭንቅላት ውስጥ የደም ዝውውርን በማፋጠን የጸጉር እድገትን ያጎለብታል
- የተጎዳ ጸጉርን በፍጥነት ይመልሳል
- ጸጉርን ያለሰልሳል
- ፎረፎርን ለማስወገድ ይረዳል
- ያለእድሜ የሚከሰተት የጸጉር ሽበት ይቀንሳል
ቅርንፉድ በቫይታሚን ኤ እና ሲ የበለጸገ መሆኑም የጸጉር ድርቀትን ለማስወገድ ይረዳል፤ የጸጉር መነቃቀልንም ያስቀራል። የጸጉር ቀለምን ጥቁር ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርገው ሜላኒን በደንብ እንዲመረት በማድረግም ያለእድሜ የሚመጣን ሸበት እንደሚያሰቀር ጥናቶች ያሳያሉ።
በመሆኑም ከቅርንፉድ የተዘጋጁ ቅባቶችን መጠቀምና በቤት ውስጥም በማዘጋጀት መጠቀም የጸጉርን ጤና ለመጠበቅ አይነተኛ ድርሻ እንዳለው ነው የተገለጸው።
የቅርንፉድ ቅባት አዘገጃጀት
- ሁለት ማንኪያ የተፈጨ ቅርንፉድ በግማሽ ኩባያ የወይራ ዘይት ውስጥ ደባልቆ ማፍላት
- ከቀዘቀዛ በኋላ ሙሉ ጸጉርን መቀባትና ለ20 ደቂቃ ማቆየት
- ከዚያም መታጠብ
የቅርንፉድ ቅባት በተለያየ መንገድ የሚዘጋጅ ሲሆን፥ በየእለቱ ቅባቱን መጠቀም ውጤታማነቱን በአጭር ጊዜ ለመመልከት ያስችላል ተብሏል።