በኢትዮጵያ በዶሮዎች ላይ በተከሰተው በሽታ የተያዘ ሰው አለመኖሩን የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ
የዶሮ በሽታ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎች የዶሮ ስጋ እና እንቁላል ባይመገቡ ይመረጣል ተብሏል
የግብርና ሚኒስቴር “የዶሮ በሽታ በኦሮሚያ እና አዲስ አበባ ተከስቷል፤ ከ50 ሺህ በላይ ዶሮዎች ሞተዋል” ብሏል
በኢትዮጵያ በዶሮዎች ላይ በተከሰተው በሽታ የተያዘ ሰው አለመኖሩን የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።
በኢትዮጵያ የዶሮ በሽታ መከሰቱን ከዚህ በፊት የግብርና ሚኒስቴር መናገሩ ይታወሳል። ሚኒስቴሩ በሽታው መከሰቱን ተናግሮ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስቦ ነበር።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ለአልዓይን እንዳሉት የዶሮ በሽታው በኦሮሚያ እና አዲስ አበባ ከተማ መከሰቱን ገልጸዋል።
በሽታው እስካሁን በቢሾፍቱ፣ በአቃቂ ቃሊቲ እና ኮልፌ ክፍለ ከተሞች መከሰቱን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው እስካሁን ከ50 ሺህ በላይ ዶሮዎች መሞታቸውን አክለዋል።
በሽታው ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይሰራጭም ልዩ ክትትል በመደረግ ላይ መሆኑን እና የሞቱ ዶሮዎችንም ሳይንሱን በጠበቀ መንገድ በማስወገድ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ በበኩላቸው እስካሁን በሽታው ተከስቷል ከተባለበት ጊዜ አንስቶ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ገልጸው እስካሁን በሰው ላይ አለመከሰቱን ተናግረዋል።
በሽታው ከተከሰተባቸው አካባቢዎች ዶሮዎች እንዳይንቀሳቀሱ ግብርና ሚኒስቴር እገዳ መጣሉ በሽታው እንዳይስፋፋ ያደርጋልም ብለዋል።
የዶሮ በሽታው በተከሰተባቸው በቢሾፍቱ፣ በአቃቂ ቃሊቲ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችም የዶሮ ስጋ እና እንቁላል ከመመገብ እንዲቆጠቡ ዶክተር መሳይ አሳስበዋል።